የዋልያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ አሠልጣኝ ከትናንቱ ጨዋታ በኋላ የሰጡት አስተያየት

የዋልያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ አሠልጣኝ ከትናንቱ ጨዋታ በኋላ የሰጡት አስተያየት

“ድክመቶቹን ለይተናል ፤ በጠንካራ ስራም እንፈታቸዋለን” ፓትሪክ ቪየራ

​የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፓትሪክ ቪየራ ቡድናቸው በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሞዛምቢክ ጋር 1ለ1 አቻ ከተለያየ በኋላ የጨዋታ ግምገማቸውን እና በኢትዮጵያው ጨዋታ መሻሻል አለበት ያሉትን ሀሳብ ሰጥተዋል።

​የአርሰናል ባለታሪክ ተጫዋች የሆኑት አሰልጣኝ ቬየራ የቴራንጋ አንበሶችን ለመምራት ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ የሞዛምቢኩ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ነበር። በካፑቶ በሚገኘው ኤስታዲዮ ናሲዮናል ዶ ዚምፔቶ በተካሄደው ጨዋታ ቪየራ የመጀመሪያ ድላቸውን እንዳያስመዘግቡ ሞዛምቢኮች ከኋላ ተነስተው አቻ መውጣታቸው አይዘነጋም። በዚህም የአስቶንቪላው አጥቂ ኒኮላስ ጃክሰን በ32ኛው ደቂቃ ላይ ጎል በማስቆጠር ሴኔጋልን መሪ ማድረግ ቢችልም ሞዛምቢክ እጅ ሳትሰጥ ከመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቅ ቀደም ብሎ በባከነ ሰዓት በጄኒ ካታሞ አማካኝነት አቻ መሆን ችላለች።

​ከጨዋታው በኋላ የተናገሩት የኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ ቡድን ሴኔጋል አሠልጣኝ የሆኑት ቪየራ በጨዋታው ያዩትን ድክመቶች ለይተው እንደወጡና ሁለተኛውን የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ ከማድረጋቸው በፊት ስህተቶቹን እንደሚያስተካክሉ ገልጸዋል።

አሠልጣኙ በአስተያየታቸው ​”በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ውጤት ይገባን ነበር። ነገር ግን ይህ የሚያሳየው መሻሻል ያለባቸው ቦታዎች እንዳሉ ነው። ጨዋታው ሙሉ በሙሉ ፍጹም እንደማይሆን ስለምናውቅ ጠንክረን መስራታችንን መቀጠል አለብን። ድክመቶቹን ለይተናል፤ በጠንካራ ስራም እንፈታቸዋለን።”

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ማክሰኞ በባህር ዳር ስታዲየም ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።