በአብዩ አረጋሽ
ፈረሰኞቹና ሰጎኖቹ ነጥብ ተጋሩ የአፄዎቹና የጦና ንቦቹ ጨዋታም በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ነገሌ አርሲ
በልዩ የደጋፊዎች ድባብና በጥሩ ፉክክር በታጀበው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ያደረጉት እና የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰው ለግብ የቀረበ ሙከራ የሚጠቀስ ሲሆን በአጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠር ሁለቱ ቡድኖች ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በ52ኛው ደቂቃ ላይ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ናትናኤል ዳንኤል ከያሬድ የማነ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም ነገሌ አርሲዎች ብዙ ሳይቆዩ በ63ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ከኮሊን ኮፊ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል። በመጨረሻም ሁለቱ ቡድኖች በየፊናቸው ባስቆጠሩት አንድ አንድ ግብ 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከተማ
በሀላባ ከተማ የጦና ንቦቹን ከ አፄዎቹ ጋር ያገናኘው
ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ የማስቆጠር ዕድል ሳይፈጠር እና አስደናቂ ሙከራ ሳይታይ አጋማሹ ተመጣጣኝ ፉክክር ተደርጎበት ያለ ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ባደረጉት ቅያሪ የጨዋታውን ፍጥነት ለመጨመርና ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት የተደረገበት ቢሆንም ጥረታቸው ወደ ግብነት ሳይቀየር የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት 0 ለ 0 ተጠናቆ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ነጥብ ወስደዋል።

