ዳኛው ለምን ከሀዲያ ተጫዋቾች ጋር አብሮ ፎቶ ተነሳ?

ዳኛው ለምን ከሀዲያ ተጫዋቾች ጋር አብሮ ፎቶ ተነሳ?

ዛሬ መነጋገሪያ ስለሆነውና ከሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ጋር የቡድን ፎቶ አብሮ ስለተነሳው ዳኛ ጉዳይ….

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት የተጠናቀቁ ሲሆን በአብዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ላይ የተገኘ አንድ ምስል በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲነጋገሩበት ሆኗል። የሶከር ኢትዮጵያ ባልደረባ የሆነው ጫላ አቤ እና በስፍራው የተገኙ ሌሎች የካሜራ ባለሙያዎች ያስቀሩት ይህ ከስር የምትመለከቱት ምስል እንደ ወትሮ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ሜዳ ላይ የሚሰለፉ የሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 11 ተጫዋቾች ብቻ ወይም የቡድኖቹ የአሠልጣኞች አባላት የተካተተበት ሳይሆን የጨዋታው አመራር ወይም ዳኛ አብሮ የሚታይበት ነው። በዚህም ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ፌዴራል ዳኛ በኃይሉ ጌታቸው ከሀዲያ ሆሳዕና የቡድን አባላት ጋር ፎቶ ተነስቷል። ታዲያ ይህ ጉዳይ ብዙዎች እንዲነጋገሩበት ያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ እርግኳስ ድምፅ የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን በሚከተለው መንገድ ግልፅ ለማድረግ ሞክራለች።

በአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም የተፈጠረው የዛሬው አጋጣሚ የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ቴሴራ ስላላለቀላቸው አራተኛ ዳኛው ማስረጃ ለመያዝ የሚያስችለውን ፎቶ አብሮ ከተጫዋቾቹ ጋር እንደተነሳ አረጋግጠናል። በእግርኳስ የዳኝነት ህግ ላይ ዳኞች የሚመሩት ጨዋታ ላይ ከሚሳተፉ ቡድኖች ወይም ተጫዋቾች ጋር ፎቶዎችን እንዲነሱ የሚያበረታታ ህግ እንዲሁም የውድድር ደንብ ባይኖርም ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ቴሴራ የሌላቸውን ተጫዋቾች ለመለየት ይሄንን ተግባር እንደሚያደርጉት አውቀናል።

መሰል አጋጣሚዎች በተለይ በሊግ አንድ እንዲሁም የእድሜ እርከን ቡድን ውድድሮች ላይ የተመለከትን ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም አልፎ አልፎ ይስተዋላል። ብዙ ጊዜ ደግሞ ሊጉ ሲጀመር እና የአጋማሽ የዝውውር መስኮት አካባቢ ቴሴራዎች ካልደረሱ ዳኞች ጨዋታ ላይ ይህንን “መላ” ሲያደርጉ ይታያል።