የዚህኛው ሳምንት ሌላኛው ትኩረታችን ደግሞ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አጥቂ መልካም ምግባር ነው።
በ3ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሃግብር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሸገር ባገናኘው ጨዋታ ከሜዳ ላይ ፉክክሩ ባሻገር ግን የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የመስመር ተጫዋች አቤል ሀብታሙ ምግባር የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አጋጣሚ ነበር።

በጨዋታ ሂደት በማጥቃት ሲሶ ውስጥ በኢትዮ ኤሌክትሪኮች ቀኝ መስመር በኩል ኳስ ያገኘው አቤል ከፊቱ ከሚገኘው ገዛኸኝ ደሳለኝ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም እሱን ለመከላከል እየተጠጋ የሚገኘው ገዛኸኝ ጉዳት ማስተናገዱን በበመልከቱ ተጫዋቹ ምንም እንኳን አደገኛ የማጥቃት አጋጣሚን ሊፈጥር የሚችልበት ዕድል ቢኖርም ከሜዳ ላይ ውጤትም በላይ የሆነውን ሰብዓዊነትን በማስቀደም ኳሷን ወደ ውጭ ያወጣበት መንገድ በጣም አስገራሚ አጋጣሚ ነበር።
ይህ ድርጊት እግር ኳስ በ90 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከማሸነፍና መሸነፍ በዘለለ ትልቅ ዓላማ ያላው ፍትሃዊነትና ሰብዓዊነት የሚቀነቀንበት መድረክ መሆኑን ዳግም ስጋ ያለበሰ አጋጣሚ ሲሆን ተጫዋቹም ስለ ድርጊቱ አድናቆት ይገባዋል።

