በኢትዮጵያ እግር ኳስ መዝገበ ቃላት መሳይ ተፈሪ የሚለው ስያሜ ለዘመናት “የተገራ ስሜታዊነት” የሚል ትርጉም ኖሮት ቢቆይም የትናንቱ የመሳይ ተፈሪ ተግባር ግን ለብዙዎች ዱብዳ የሆነ ክስተት ነበር።
ያለ በቂ እግር ኳሳዊ ሀሳብ ኳስን ተቆጣጥረን በመጫወት ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን እንገነባለን የሚሉ አሰልጣኞች በሞሉበት ሊጋችን ከፍ ባለ ተነሳሽነት የሚጫወቱ የራሳቸው መገለጫ ያላቸው ቡድኖች በመገንባት የሚታወቁት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከዓምናው የውድድር ዘመን አጋማሽ አንስቶ የቀድሞ ክለባቸውን ወላይታ ድቻን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ።
መሳይ ከስልጠናው ባሻገር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተጫዋችነት ሆነ ወደ ስልጠና ከተሸጋገሩ በኋላ በላቀ ስብዕናቸው የሚታወቁ ቢሆንም ትናንት በሊጉ ቡድናቸው በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በባህር ዳር ከተማ 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ግን ያሳዩት ምግባር መሳይ ተፈሪን ፈፅሞ የማይመስል ነበር።

ለወትሮው በሜዳው ጠርዝ በቁንጥንጥነት እና “በተገራ ስሜታዊነታቸው” የሚታወቁት አሰልጣኙ ቡድናቸው መመራቱን ተከትሎ በተለይ በባህር ዳር ከተማዎች በኩል ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ እና ሌሎች ተጫዋቾች ጊዜ እያባከኑ ነው በሚል በተደጋጋሚ ወደ አራተኛ ዳኛው ጥላሁን ሙሉጌታ በማምራት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቢቆይም በዚህ የቃላት ልውውጥ መካከል ነገሮች በመካረራቸው አሰልጣኙ ከሜዳ ጠርዝ በቀይ ካርድ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።
ከቀይ ካርዱ በኋላ ከጨዋታ አመራሮቹ ጋር ለፀብ የተጋበዙት መሳይ ተፈሪ ተጫዋቾቹ ሆነ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሊያረጋጓቸው ሲሞክሩ ለያዥ ለገላጋይ አስቸግረው የተመለከትናቸው ሲሆን ይህ የአሰልጣኙ ድርጊት ብዙኀኑን የስፓርት ቤተሰብ ከማሳዘን ባለፈ ይህን ሂደት ተከትሎ ጨዋታው ለሦስት ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ምክንያት የነበረ አጋጣሚ ነበር።
በዚህ መነሻነት ከሰዓታት በፊት አሰልጣኙ የ10 ጨዋታ እና 10 ሺህ ብር ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን ከመሪነት ፣ ታክቲካዊ ልህቀት እና ተግባቦት ባለፈ በምሳሌነት መምራትን በሚጠይቀው ሙያ ውስጥ እንደመገኘታቸው አሰልጣኙ መላውን የስፓርት ቤተሰብ ተምሳሌታዊ ስላልሆነ ምግባራቸው የተከፉትን መላውን የስፓርት ቤተሰብ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል።

