በሀገሪቱ ትልቁ የክለቦች መድረክ አንድ ተጫዋች ከአንድ ሰዓት ለሚልቁ የጨዋታ ደቂቃዎች በተቀደደ መለያ…
ብዙ አሉታዊ ጉዳዮች በሚነሳበት እግር ኳሳችን በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተመለከትናቸው መሻሻሎች አንዱ የክለቦቻችን የትጥቅ አቅርቦት ጉዳይ አንዱ ነው ፤ በቀደሙት ዓመታት የራሳቸው መገለጫ የሆኑ መለያዎች (Custom Kit) ያላቸውን ክለቦችን ፈልጎ ማግኘት ከባድ በነበረበት ሊጋችን አሁን ሁሉም ክለብ በሚባል ደረጃ ራሱን የሚገልፅ መለያ መጠቀም የቻለበት ፣ ደጋፊዎች እንደልባቸው የሚደግፉትን ክለብ ማልያ ማግኘት የጀመሩበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
በሀገር በቀል ተቋማት ሙሉ ለሙሉ እየተዘወረ በሚገኘው የሊጋችን ትጥቅ አቅርቦት ዙርያ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁን ድረስ ግን ኢንደስትሪው ያልተሻገራቸው የጥራትና የንድፍ(Design) ችግሮች ይስተዋላሉ ፤ በተለይ በተጫዋቾች የጨዋታ ዕለት እንቅስቃሴ (Performance) ላይ አይነተኛ ተፅዕኖ ባለው ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ኢንደስትሪው አሁን ድረስ ያልተሻገረው ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
አሁን ላይ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመሩ የመጡት የሀገር በቀል ትጥቅ አምራች ተቋማት መበራከት በበጎ ጎኑ የሚነሳ ቢሆንም እነዚህ ተቋማት በኢንደስትሪው ውስጥ ከቆዩ ተቋማት ትምህርትን ወስደው ኢንደስትሪውን ሊያሻግሩ የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦችን በገበያ አረዳድ ፣ በምርቶች ጥራት እንዲሁም በማርኬቲንግ ስትራቴጂ ይዘው ከመምጣት ይልቅ ተሞክሮ ሰርቷል የተባለው መንገድ መጓዝን ቢመርጡም እንደው የተሻለ ነገር መፍጠር ባይችሉ እንኳን የነበሩትን መምሰል ግን ተቸግረው እያስተዋልን እንገኛለን።
በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ የጨዋታ ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከአዳማ ያገናኘውና በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ወቅት ያስተዋልነው ሁነትም የዚህ ማሳያ ነው።
በመጀመሪያው አጋማሽ 30ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቢላል ገመዳ እየነዳ አዳማ ሳጥን ውስጥ ያደረሰውን ኳስ ለመከላከል ጥረት ያደረገው ሙጂብ ቃሲም ኳሷ ወደ ውጭ ስትወጣ የመጨረሻው ንክኪ የአንተ ነው በሚል የተሰጠባቸውን የማዕዘን ምት በመቃወም በብስጭት ማልያውን በሚጨብጥበት ወቅት መለያው የተቀደደበት አጋጣሚ ትኩረትን የሳበ ነበር።

እርግጥ በእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ የተጫዋቾች መለያ የመቀደድ ጉዳይ አስገራሚ ነገር ባይሆንም ይህን አጋጣሚ የተለየ የሚያደርገው ሙጂብ ከተቃራኒ ተጫዋች ጋር አካላዊ ፍትጊያ ውስጥ ሳይገባ በገዛ እጁ በቀላሉ መለያውን አንገቱ አካባቢ ሲስበው የመከሰቱ ጉዳይ እንጂ።
መለያው ከመቀደዱ ባሻገር ታድያ ተጫዋቹ ቀሪ የመጀመሪያውን አጋማሽ አስራ አምስት ደቂቃዎች በተቀደደው መለያ እንዲያጠናቅቅ የመገደዱ ጉዳይ ሌላው አስተዛዛቢ ጉዳይ ሲሆን ይባስ ብሎ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ወደ ሜዳ ሲመለስ ደግሞ ሙጂብ በሌላ መለያ ይቀርባል ብለን ስንጠብቅ መለያውን ከመቀየር ይልቅ የተቀደደውን መለያ በፕላስተር ተጀብኖ ወደ ጨዋታ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን በአሳዛኝ ሁኔታ በጨዋታው ሂደት የተለጠፈው ፕስተር ለቆ ሙጂብ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ 15 ደቂቃዎች ሁሉ ደረቱ በተቀደደ መለያ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገዷል።
ሊጋችን ስታዲየም ከሚታደሙ ሺዎች ባሻገር ዓለምአቀፍ ስርጭት ማግኘትን በተለማመደበት በዚህ ወቅት መሰል አንገት አስደፊ ክስተቶችን መመልከት ልብ የሚሰብር ሲሆን ክለቦቻችን አልፍ ሲል እግር ኳሳችን ውስጥ ያውን ከሙያተኝነት (professionalism) እሳቤ የተፋታ ኃላ ቀር እሳቤ አይነተኛ ማሳያ ነው።
በሌላው ዓለም ቡድኖች በጨዋታ ዕለት ለእያንዳንዱ ተጫዋች ለብሰው የሚገቡትን መለያ ጨምሮ ለእያንዳንዱ ተጫዋች ሦስት መለያዎች በጨዋታ ዕለት ዝግጁ የሚያደረጉ ሲሆን እንደ ሙጂብ አይነት አጋጣሚዎች ሲገጥሙ ሆነ ሌሎች አስገዳጅ መለያ የሚያስቀይሩ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ያለ ስጋት መቀየር የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራሉ።
እንደው እንደ ውጪዎቹ ሦስት መለያ መያዝ ቅንጦ ቢሆን እንኳን ቁጥርና ስም ያልተፃፈባቸው የተወሰኑ ተጠባባቂ መለያዎች ቢኖሩ ለቀሪ የጨዋታ ደቂቃዎች እንደነገሩ በጊዚያዊ መንገዶች የተጫዋቹ ቁጥር ተፅፎበት ጨዋታውን ማጠናቀቅ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር በተቻለ ነበር።
እግር ኳሳችን አሁንም ምንም እንኳን በአመዛኙ ከመንግሦት ቋት በሚገኝ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም በተለይ በላይኛው እርከን የገንዘብ ችግር ባይኖርም ያለን አቅም በአግባቡ እና በዘላቂታዊነት ጥቅም ማስገኘት በሚችሉ መስኮች ላይ ማዋል ባለመቻላችን ክለቦቻችን ሁሌም እንደ መለያው ሁሉ ከዛሬ የሚሻገር ጥሪት ሳይኖራቸው እየተንገዳገዱ ስለነገ ራሱ ነገ ያውቃል ብለው ለዛሬ ብቻ እየኖሩ በኃላ ቀሩ መንገድ ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

