መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መምራት ጀመረ

መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መምራት ጀመረ

በአብዩ አረጋሽ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መጨረሻ ቀን ጨዋታ መቻል ኢትዮጵያ መድንን 3ለ1 በማሸነፍ በ9 ነጥብ ሊጉን መምራት ጀምሯል

በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀን 9:00 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ መቻል በ10ኛው ደቂቃ መሪነቱን የያዘ ሲሆን መሐመድ አበራ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ቀሪው የመጀመሪያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ መቻል የበላይነቱን ያስቀጠለ ሲሆን በ57ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ እንዳለ ዮሐንስ በኮነህ ጀግባይ ላይ የሰራው ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፈቱዲን ጀማል ወደ ግብነት በመቀየር መሪነቱን ወደ 2ለ0 አሳድጓል።

በ90ኛው ደቂቃ መሐመድ አበራ ለመቻል ሦስተኛውን ግብ በማስቆጠር የድሉን ልዩነት አስፍቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ያሬድ ብርሃኑ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ኦሊሳ በግንባሩ በመግጨት ለኢትዮጵያ መድን የማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በመቻል 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።