“እኔ ድሮ እንደዚህ አይነት ጎል ሲገባ የማውቀው የወረዳ ፤ የቀበሌ ጨዋታ ላይ ነው። ግብ ጠባቂው ይጠልዛል ሄዶ አጥቂው ያገባል…” በሚል አነጋጋሪ አስተያየት ሰጥተው የነበሩት በኋላም በይፋ ይቅርታ የጠየቁት የሸገር ከተማው አሠልጣኝ ጉዳይ የጨዋታ ሳምንቱ የትኩረታችን መጀመሪያ አድርገነዋል።

ከትናንት በስትያ በሸገር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል በተደረገው ተጠባቂ መርሐ-ግብር የሸገሩ አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት አስተያየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ያስቆጠረው ግብ ከተጋጣሚ ግብ ጠባቂ በረዥሙ በተመታ ኳስ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ በስላቅ የተሰነዘረው ይህ አነጋገር የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በአስተያየት ሰጪው በኩል በፍጥነት በመታረሙ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንዲሁም ለቡድን አባላት ይቅርታ በመጠየቁ ቀድመን ለማውጣን ያዘጋጀነውን ፅሁፍ በመቀየር ንግግሩ ምን ሊያስተምረን እንደሚችልና በፍጥነት ጥፋቱን በይቅርታ የመሻሩን መልካምነት ለማንሳት ወደናል።
በእግር ኳስ ማዕበል ውስጥ ሆነው ስሜታዊ በሆኑ ሰዓታት የሚሰጡ አስተያየቶች ወደ ስላቅ ሊወስዱ ይችላሉ ፤ ነገር ግን ስህተትን አምኖ መቀበል እና ይቅርታ መጠየቅ የትልቅ ባለሙያ መገለጫ ነው። የሸገር ከተማው ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር እያሱ የተናገሩትን ቃል በማስተካከልና ይቅርታ በመጠየቃቸው የስፖርታዊ ትስስርንና መከባበርን በማሳየት ረገድ አርአያነት ያለው እርምጃ ወስደዋል። ይህ አካሄድ በእርሳቸው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በክለቦቹ በደጋፊዎች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አላስፈላጊ መሻከር በማቀዝቀዝ ሊጉ በሰላም እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አስተያየቱ መታረሙ እንደተጠበቀ ሆኖ ግ በታላላቅ መድረኮች የረዥም ኳስን (Long Ball Distribution) በተመለከተ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ስፔን ላሊጋ እና ቻምፒዮንስ ሊግ ባሉ ከፍተኛ መድረኮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከግብ ጠባቂ እግር ወይም እጅ በረዥሙ የሚነሱ ኳሶች የጨዋታው ዋነኛ የማጥቂያ አካል ናቸው። በታላላቆቹ ሊጎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከግብ ጠባቂ በረዥሙ ተነስተው ከሚላኩ ኳሶች ውስጥ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት በቀጥታ ወይም በሰከንዶች ውስጥ ለሚፈጠሩ አደገኛ የግብ ዕድሎች ምክንያት ይሆናሉ። በተጨማሪም ቁጥሮች እንደሚያሳዩት በታላላቆቹ ሊጎች ከሚቆጠሩ ግቦች ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከአምስት ሰከንዶች ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከግብ ጠባቂ ኳስ ተጀምሮ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚደርሱ የፈጣን ሽግግር (Fast Counter-Attack) ውጤቶች ናቸው።
በዘመናዊው እግር ኳስ ግብ ጠባቂዎች ኳስን ማዳን ብቻ ሳይሆን እንደ መጀመሪያው አጥቂ (Deep-lying playmaker) በመሆን ቡድናቸውን የማዋቀር ሚና አላቸው። እንደ ቀድሞው የማንቸስተር ሲቲው የግብ ዘብ ኤደርሰን እና የሊቨርፑሉ አሊሰን ያሉ ዘመናዊ ግብ ጠባቂዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ሆነው በረዥሙ የሚልኳቸው ኳሶች ለክለባቸው በርካታ ድል አስገኝተዋል ፤ ኳሱን በረዥሙ መምታት ዕድል ሳይሆን የተለማመዱት የታክቲክ ስልት ውጤትም ነው። እንደ ሪያል ማድሪድ እና ሊቨርፑል ያሉ ክለቦች አጥቂዎቻቸው ግብ ጠባቂው ኳስ በረዥሙ እንደሚመታ አስቀድመው በማሰብ የተሻለ ቦታ አያያዝ እንዲኖራቸው በስልጠናው መድረክ ይሠሩበታል። ታዲያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገኘው ጎል የዚህ የሰለጠነ የሜዳ ላይ ንቃት ውጤት እንጂ “የቀበሌ ጨዋታ” የሚያስብል አይደለም።
ልምድ እና እውቀት ካላቸው አሠልጣኞች የሚጠበቀው ምላሽ ከሰበብ ፖለቲካ የጸዳ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ታላላቅ አሠልጣኞች ከጨዋታ በኋላ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ከስላቅ እና ከሰበብ የፀዱ በመሆናቸው ይታወቃሉ። እንደ ፔፕ ጓርዲዮላ ወይም ማይክል አርቴታ ያሉ አሠልጣኞች ቡድናቸው በረዥም ኳስ ወይም በግድየለሽነት ጎል ሲያስተናግድ ጎሉ የገባበትን መንገድ ከማጣጣል ይልቅ ተከላካዮቹ ሁለተኛውን ኳስ ለመቆጣጠር እና የኋላ መስመር ሽፋን ለማድረግ ለምን እንዳልቻሉ በሰከንድ በሰከንድ ይተነትናሉ። የተጋጣሚን ጥረት እና የተገኘውን ግብ ማጣጣል የደጋፊውን ስሜት ለጊዜው ሊያረጋጋ ይችላል እንጂ የራሱን ተጫዋቾች ተነሳሽነት እና የቴክኒክ ቡድኑን ስራ ወደፊት አያራመደውም። የእኛም ሀገር አሠልጣኞች የራሳችን የጨዋታ መንገድ ምን ይመስላል? የሚለውን ሀሳብ ሳናነሳ እንኳን ከላይ ባልነው መንገድ ግቦች የተቆጠሩበትን መንገድ በባለሙያ ዐይን አይቶ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይህም የዶ/ር እያሱ ተግባር ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሊጉ አሠልጣኞችም ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ተግባር ነው።
እግር ኳስ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ሲመጣ ማስተዋል የሚገባን ዋናው ጉዳይ ኳሱ ከየት ተነሳ የሚለው ሳይሆን በሜዳ ላይ በተፈጠረ ቅንጅት አጋጣሚው እንዴት ወደ ግብ ተቀየረ የሚለው ነው። የሸገር ከተማው አሠልጣኝ ስህተታቸውን አምነው በመቀበልና ይቅርታ በመጠየቅ ያሳዩት ብስለት የሚወደስ ነው። ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም እኛም ሀገር ያሉ ክለቦችም ሆኑ አሠልጣኞች የረዥም ኳስ አጠቃቀምን እንደ አንድ ታክቲክ በመረዳት እና ስፖርታዊ ወንድማማችነትን በማስቀደም ሊጉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚችሉ ሊያጤኑ ይገባል።

