ካፍ የ2028፣ 2031 እና 2033 የአፍሪካ ዋንጫ የሚያስተናግዱ ሀገሮችን ለመምረጥ የአመልካቾችን የእጩነት ምዝገባ በድጋሜ በይፋ መክፈቱ ታውቋል።

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የ2028፣ የ2031 እና የ2033 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮችን ለማስተናገድ ለሚፈልጉ ሀገራት የጨረታ እና የእጩነት ምዝገባ ሂደቱን በድጋሚ መክፈቱን በይፋ አስታውቋል። ይህ ውሳኔ ይፋ የሆነው የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኦክቶበር 29 ባካሄደው ስብሰባ ውድድሩን በየአራት ዓመቱ ለማድረግ ተይዞ የነበረውን ቀዳሚ እቅድ በመሰረዝ ወደ ነበረበት በየሁለት ዓመቱ የመካሄድ ዑደት እንዲመለስ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን ተከትሎ ነው።
በተሻሻለው አዲሱ የውድድር ካሌንደር መሰረት የ2028ቱ ውድድር በቀድሞው ዓመቱ እንዲቀጥል ሲደረግ ቀደም ሲል በ2032 እና በ2036 እንዲካሄዱ ታቅደው የነበሩት ውድድሮች ወደ 2031 እና 2033 እንዲሳቡ ተደርጓል። ካፍ ይህንን ማሻሻያ ሲያደርግ ሞሮኮ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በጣምራ የምታስተናግደውን የ2030 የፊፋ የዓለም ዋንጫ መርሐ-ግብር ታሳቢ ማድረጉም ተገልጿል። ከዚህም ባለፈ ውድድሩን በየአራት ዓመቱ ለማድረግ እና ይህንንም ለመደገፍ ታስቦ የነበረው አዲሱ “የአፍሪካ ኔሽንስ ሊግ” በቂ የፋይናንስ አቅም ለመገንባት ተጨማሪ ጊዜ ስለሚያስፈልገው ማኅበሩ የቀድሞውን የሁለት ዓመት ዑደት መመለስን መርጧል።
የጨረታው ህጎች እና የተሳታፊ ሀገራት ዕድልን በተመለከተ ካፍ ኖቬምበር 6 ለሁሉም 54ቱ አባል ፌዴሬሽኖች በላከው የውስጥ መመሪያ መሰረት በቀደመው ዙር ፍላጎት ያላሳዩ ሀገራትን ጨምሮ ሁሉም አባል ሀገራት በዕጩነት የመወዳደር እድል ተሰጥቷቸዋል። ቀደም ሲል የፍላጎት መግለጫ (Declaration of Interest) ያስገቡ ፌዴሬሽኖች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በድጋሜ ማስገባት እንደማይጠበቅባቸው ተገልጿል። አመልካች ሀገራት ውድድሩን በተናጥል ወይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለማስተናገድ ማመልከት የሚችሉ ሲሆን ከአንድ በላይ የውድድር ዓመታትን ለማስተናገድም ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል ተመላክቷል። ካፍ ሁሉም ማመልከቻዎች በእኩል መስፈርት እንደሚገመገሙና በቀደመው ዙር መሳተፍ ምንም ዓይነት ልዩ ብልጫ እንደማያስገኝ አጽንኦት መስጠቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዚህም መነሻነት በካፍ መመሪያ መሰረት ውድድሩን የማስተናገድ ሂደት በተመለከተ ወሳኝ የጊዜ ሰሌዳዎች እና መስፈርቶች በግልጽ ተቀምጠዋል። በዚህም ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ያላቸው አዲስ አመልካች ሀገራት የፍላጎት መግለጫቸውን እስከ ኖቬምበር 17 2026 ድረስ ማስገባት ይኖርባቸዋል። በመቀጠልም ፌዴሬሽኖች ከመስተንግዶ መስፈርቶች ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ዓይነት ማብራሪያ የሚጠይቁበት የመጨረሻ ቀን ኖቬምበር 24 ሲሆን ተወዳዳሪ ሀገራት ዝርዝር የጨረታ ሰነድ (Bid book)፣ የመንግስት ዋስትናዎች፣ የተፈረሙ የመስተንግዶ ስምምነቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ህጋዊ ሰነዶችን አሟልተው የሚያስገቡበት የመጨረሻ ቀን ዲሴምበር 8 2026 መሆኑ ተገልጿል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወቅ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀድማ ያስገባችው ሰነድ እንደሚታይ የሰማን ሲሆን እንደ አዲስ ሌላ ተጨማሪ ሰነድም የማስገባት ፍላጎት ካላት በሩ ክፍት እንደሆነ እንዲሁም ከ2028 የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሌላ ዓመት ማለትም የ2031 ወይም 2033 ውድድር ፍላጎት ካላት ሰነዷን መቀየር እንደምትችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

