በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ባለው ፉክክር ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑትን ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማን በአዲስ አበባ ስታድየም ያገናኘው ጨዋታ 11፡30 ላይ ነበር የጀመረው።
የሹፌሮች ቀን በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ሹፌሮች ማህበር አማካይነት እየተከበረ መሆኑን በማስመልከትም ከጫወታው መጀመር በፊት በሀገራችን በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ታስበዋል ።
ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረ ጀምሮ ሳይወርዱ በሊጉ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች በሚገናኙባቸው ጨዋታዎች መልካም የመሸናነፍ ፉክክር ከበርካታ ግቦች ጋር መመልከት የተለመደ መሆኑ ላይ ቡድኖቹ አሁን ካሉበት ሁኔታ አንፃር 3 ነጥቡ እጅግ አስፈላጊያቸው መሆኑ ተጨምሮበት ጨዋታውን ጥሩ ግምት አሰጥቶታል። እንደተጠበቀውም በተለይ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጥሩ የጫወታ ፍሰት እና ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማየት ተችሏል።
በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጨዋታውን የጀመሩት እንግዶቹ ሀዋሳዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ጎል በመድረስ ቅድሚያውን ወስደዋል። በ6ተኛው ደቂቃ ላይም የሀዋሳ የመሀል ክፍል ተሰላፊዎች የተቀባበሉትን ኳስ ኳስ ፍሬው ሰለሞን ሲያሾልክለት የፊት አጥቂዎ ጃኮ አራፋት ከመጠቀሙ በፊት ሱሊማን ኤቡ ደርሶ አምክኖበታል። ሌላው አማካይ ታፈሰ ሰለሞንም ከ አንድ ድቂቃ በኋላ ከሳጥን ውጪ ሌላ ሙከራ አድርጎ በግቡ አናት ወጥቶበታል ።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ኤሌክትሪኮችም በ15ኛው ደቂቃ በግራ መስመር አጥቂነት የተሰለፈው ፍፁም ገ/ማርያም ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ይዞ በመግባት ባደረገው እና ወደውጪ በወጣበት ሙከራ ነበር የሀዋሳዎችን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ሀዋሳዎች ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በጋዲሳ መብራቴ አማካይነት ከግራ መስመር ላይ ያሻሙት ኳስ ጃኮ አራፋት በግንባሩ ሳይደርስባት ቀረ እንጂ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበረች ።
በፍጥነት የታጀበው ጨዋታ ሌላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሊያሳየን የፈጀበት ጊዜ 1 ደቂቃ ብቻ ነበር። ይኅውም አጋጣሚ የተፈጠረው በቀኝ መስመር ሙሉአለም ጥላሁን ያገኘውን አጋጣሚ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ለፍፁም ለመስጠት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ወጣቱ የሀዋሳ የመሀል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ሲያወጣበት ነበር ። ሆኖም ኤሌክትሪኮች በ18ተኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ገ/ማሪያም አማካይነት ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ጓሏም ቡድኑ በቀኝ መስመር በሰነዘረው ጥቃት ዳዊት እስጢፋኖስ ከሙላለም ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲጥልለት በግቡ አካባቢ ይገኝ የነበረው አጥቂ ፍፁም ገ/ማርያም በጥሩ አጨራረስ ያስቆጠራት ነበረች።
ከጓሏ መቆጠር በኋላም ወደፊት ለመሄድ ያልቦዘኑት ሀዋሳዎች በ22ኛው ደቂቃ በፍሬው ሰለሞን አማካይነት ከግራ መስመር በተሻገረ ኳስ ሌላ እድል ቢያገኙም ሱሊማን ኤቡ አውጥቶባቸዋል ። ዳንኤል ደርቤም የተመለሰውን ኳስ አግኝቶ ቢሞክርም ኢላማውን መጠበቅ አልቻለም ።
ዳንኤል ደርቤን እና ጋዲሳ መብራቴን በመስመር ተመላላሽነት ሚና በመጠቀም ከኋላ 3 የመሀል ተከላካዮችን ይዘው የገቡት ሀዋሳዎች በመሀል ተከላካዮቹ እና በመስመር ተመላላሽምቹ መሀከል በሁለቱም አቅጣጫዎች በኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂዎች የደረሰባቸውን ጥቃት ተከትሎ ይመስላል አንዱን የመሀል ተከላካይ መላኩ ወልዴን በመስመር አጥቂው ዮናታን ከበደ ቀይረው አስወጥተዋል። በዚህም ሁለቱ የመስመር ተመላላሾች ሚና ወደመስመር ተከላካይነት ተቀይሮ ቡድኑ ከኋላ በ አራት ተከላካዮች መጠቀም ጀመረ ። ሆኖም ግን ከዚህ ቅያሪ በተመሳሳይ ቅፅበት ከዳዊት እስጢፋኖስ የተላከች ድንቅ ኳስ በፍፁም ገ/ማርያም የቺፕ አጨራረስ በሳሆሆ ሜንሳህ አናት ላይ አልፋ ለኤሌክትሪክ ሁለተኛ ጎል ሆነች።
በ2-0 መሪነት ወደመልበሻ ክፍል የገቡት ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ግማሽ በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄን መርጠው የገቡ ይመስሉ ነበር። ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ቡድኑ ከመጀመሪያው አጋማሽ ያነሰ የማጥቃት ጥረት ሲያደርግ ታይቷል።
የጨዋታ ቅርፅ ለውጥ ያደረገው ሀዋሳም በጨዋታው ጅማሮ በመስመር ተመላላሾቹ አማካይነት የሜዳውን ስፋት ይጠቀም የነበረ ቢሆንም ከለውጡ በኋላ የቡድኑ አጨዋወት ወደመሀል ጠቦ በጣም ተቀራርበው ከሚጫወቱት የመስመር አጥቂዎቹ እና የመሀል አማካዮቹ የሚገኙት እድሎች ለጎል ቢቀርቡም በቂ የመጫወቻ ክፍተት በማጣት በተደጋጋሚ ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል፡፡
ሀዋሳዎች በጣም ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚም በ65ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ከበደ ከቀኝ መስመር የተሻገረ ኳስ በኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌማን አቡ እና በግራ መስመር ተከላካዩ አለምነህ ግርማ አለመናበብ የተገኘ ቢሆንም በቦታው የነበሩ የሀዋሳ ተጨዋቾች ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በ71ኛው ደቂቃ ላይ አዲስአለም ተስፋዬ ተቀይሮ በገባው የኤሌክትሪክ አማካይ በሀይሉ ተሻገር ላይ በፈፀመው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከማዳ ከወጣ በኋላ የሀዋሳዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተዳክሞ ታይቷል ። ቡድኑም ኤፍሬም ዘካሪያስ በ76ተኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ40 ሜትር ርቀት ከሞከረው ኳስ ሌላ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ አልቻለም።
የቁጥር ብልጫ ያገኙት ኤሌክትሪኮችም ከቀይ ካርዱ በኋላ የተሻለ ወደፊት ገፍተው የማጥቃት ሙከራዎችን ለምድረግ ጥረዋል ። ነገር ግን በተደጋጋሚ በሚታዩ ያልተመጠኑ ኳሶች እና ከጫወታ ውጪ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ሶስተኛ ጎል ማግኘት አልቻሉም። ወደጨዋታው መገባደጃ ላይ ፍፁም ግ/ማርያም በግራ መስመር ተነስቶ ወደ ሀዋሳ ጎል በመቅረብ አክርሮ የመታው እና ሳሆሆ ሜንሳ ያወጣበት ኳስ የቡድኑ ከባድ ሙከራ ነበር ። ነገር ግን ምንም እንኳን የጎል መጠኑን መጨመር ባይችሉም ኤሌክትሪኮች ውጤቱን በማስጠበቅ ጨዋታውን በድል ጨርሰዋል። በዚህም መሰረት ባገኘው 3 ነጥብ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በ11 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል ።