ካሜሩን 2019 | ዋልያዎቹ በሜዳቸው ነጥብ ጥለዋል

ለ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኬንያ፣ ጋና እና ሴራሊዮን ጋር የተደለደሉት ዋሊያዎቹ ዛሬ የምድብ ሶስተኛ ጨዋታቸውን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም አከናውነው ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

በአስደማሚ የደጋፊ ድባብ ታጅቦ በተከናወነው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድሎችን በአግባቡ ወደ ግብነት የመቀየር ችግር የታየባቸው ሲሆን በአንፃራዊነት በመጀመሪያው አጋማሽ ኬንያ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ኢትዮጵያ ብልጫ ወስደው ተንቀሳቅሰዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን እንዲሁም የአማራ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወለላን ጨምሮ በክብር እንግድነት በሜዳው ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉት ሲሆን ከባህር  ዳር ከተማ ውጪ ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ የስፖርት ቤተሰቦች ሞቅ ያለ  ድጋፍ ጨዋታው ተከናውኗል።


በ4-2-3-1 የተጨዋች አደራደር ወደ ሜዳ የገቡት የዋሊያዎቹ አለቃ አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) ጷግሜ 3 ከተደረገው የሴራ ሊዮን ጨዋታ ኡመድ ዑኩሪን በዳዋ ሆቴሳ በመቀየር ቡድናቸውን ወደ ሜዳ ልከዋል። በ39 ዓመቱ ጋንቢያዊው ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ በተመራው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በስታዲየም ሲሰጥ እንደነበረው ሞቅ ያለ ድጋፍ ተሟሙቆ የነበረ ቢሆንም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን መቀዛቀዞች ታይተውበታል።

ጨዋታው እንደተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ቢኒያም እና ሽመልስ ተቀባብለው ለጌታነህ ያሳለፉለትን ኳስ ጌታነህ ገና በጊዜ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ኳሷን ወደ ግብ ቢመታትም የኬንያ ተከላካዮች በትክክለኛው ሰዓት በቦታው ስለነበሩ ኳሷን ወደ ውጪ አውጥተዋታል። ይቺ ሙከራ በኢትዮጵያዎች በኩል ከተሰነዘረች በኋላ በደቂቃዎች ልዩነት ከኬንያዎችም በኩል ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎችን ተደርገዋል። ይህም በ3ኛው እና በ4ኛው ደቂቃ በሚኬል ኦሉንጋ የተደረገው ነው። ተጨዋቹ በመጀመሪያው ሙከራው ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሳምሶን  ያወጣበት ሲሆን በሁለተኛው ደግሞ ከመዓዘን የተሻገረችውን ኳስ እንደምንም በሰውነቱ ገጭቷት ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። 

በአስደሳች ድባብ የቀጠለው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግን የነበሩት አካላዊ ንክኪዎች መበራከት ድባቡን ሸፍኖታል። በ16ኛው ደቂቃ ከአብዱልከሪም ፊት የተሰለፈው ዳዋ ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ጎል ለመቀየር ሲሞክር ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ለዋሊያዎቹ ተከላካዮች ፈተና የነበረው ሚኬል ኦሉንጋ ከአስቻለው እና አንተነህ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አምክኖበታል። ተከላካዮችን ማስጨነቅ የቀጠለው ይህ ግዙፍ አጥቂ በ25ኛው ደቂቃም ሌላ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 


በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ኬንያዎች አሁንም ጫና ማድረጋቸውን ቀጥለው በ27ኛው ደቂቃ በኤሪክ ጆሃና ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።  ሆኖም የኤሪክን ኳስ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አድኗታል። ከደቂቃ በኋላ ለደረሰባቸው ጥቃት ወዲያው ምላሽ የሰጡት ዋሊያዎቹ አስቆጪ የግብ ማግባት ሙከራ በሽመልስ በቀለ አድርገዋል። በግራ መስመር አብዱልከሪም ለዳዋ ያቀበለውን ኳስ ዳዋ ለሽመለስ አቀብሎት ሽመልስ ኳሷን ወደ ግብ መትቶ ኢላማዋን በመሳት የግቡን መረብ ነክታ ወደ ውጪ ወታለች። በመጀመሪያው አጋማሽ በቀኝ መስመር አድልተው ሲያጠቁ የነበሩት ዋልያዎቹ በተለይ በዳዋ እና በሽመልስ አማካኝነት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ለማድረግ ሲጥሩ ነበር። 
እንደ አጀማመሩ ሳይሆን የቀረው ጨዋታው ከ27ኛው ደቂቃ ሙከራ በኋላ የግብ አጋጣሚዎችን ለማስተናገድ 16 ደቂቃዎችን ወስዶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የኬንያ አጥቂ ኦሉንጋ አስቻለው ታመነን ቀምቶ ግብ ያስቆጠረ ቢሆንም የእለቱ የመሃል ዳኛ ኳሱን ለማግኘት ጥፋት ሰርተሃል በማለት ጎሉን ሽረውታል። 


በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የአጨዋወትም ሆነ የተጨዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ በመግባት ሁለቱም ኳስን ለመቆጣጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ነገር ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ዋሊያዎቹ ሙከራዎችን በተከታታይ ያደረጉ ሲሆን ፍሬ ግን ማፍራት አልቻሉም።
በ53ኛው ደቂቃ ዋሊያዎቹ ሌላ አስቆጪ እድል ሲያገኙ አጋጣሚውን ግን ለመጠቀም ተሸግረው እድሉን አምክነውታል። ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ የነበረው ጌታነህ ለሽመልስ የሰጠውን ኳስ ሽመልስ ወደ ሞክሮ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተዋታል። አሁንም ግብ ለማስቆጠር የጣሩት የአሰልጣኝ አብርሃም ልጆች በ60ኛው ደቂቃ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ ጋቶች በግምባሩ ቢገጨውም አደጋ መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። 
ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ ዋልያዎቹ ሁለቱንም መስመሮች በመጠቀም ለማጥቃት ሲጥሩ በተለይ ኡመድ ቢኒያምን ቀይሮ ከገባ በኋላ ለቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የተለያዩ አማራጮችን ሲሰጥ ተስተውሏል። በ66ኛው ደቂቃ ከጌታነህ ጀርባ ከጋቶች እና ሙሉዓለም ፊት ተሰልፎ የነበረው ሽመልስ ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ መትቶ የግቡን ቋሚ ጨርፋ የወጣችበት ሙከራ የጨዋታው አስቆጪ ሙከራ ነበር። 

የኡመድ ቅያሪ ቡድኑን ያነቃቃው በሚመስል መልኩ ዋሊያዎቹ  አሁንም ሙከራ ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ70ኛው ደቂቃ ራሱ ኡመድ በአክሮባት ምት ሞክሮ ተከላካዮች ያወጡበት እንዲሁም ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ከቅጣት ምት ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን በኡመድ እና በጌታነህ አማካኝነት የሞከሯቸው ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ሙከራዎች በኋላ ዋልያዎቹ በሙሉ ሃይላቸው ጥቃቶች በተለያዩ አቅጣጫዎች የሰነዘሩ ቢሆንም አንዱም ግን ወደ ግብነት ለመቀየር ተስኗቸው ወጥተዋል።



በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኬንያዎች ያገኙትን ውድ አንድ ነጥብ ላለማጣት በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ሲጫወቱ የነበረ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት አንዳንድ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም በዚህ አጋማሽ ግልፅ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም።
ሁለቱ ቡድኖች ከአራት ቀናት በኋላ በመጪው ሰኞ ናይሮቢ ላይ የምድቡ አራተኛ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።