የሊጉ መርሃግብር ከቀናት ዕረፍት በኋላ ዛሬ ሲመለስ ሰሑል ሽረን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በ26ኛው ሳምንት ስሑል ሽረዎች ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ውስጥ ጃዕፋር ሙደሲር እና ፋሲል አስማማውን አሳርፈው በኤልያስ አህመድ እና ብሩክ ሀዱሽ በመተካት ለጨዋታው ሲቀርቡ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ባልተለመደ ሁኔታ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው አብነት ሀብቴ፣ ኬኔዲ ከበደ፣ አዛሪያስ አቤል፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ ያሬድ ደርዛ እና ካርሎስ ዳምጠውን በግብ ጠባቂ ቢንያም ገነቱ፣ ናትናኤል ናሲሮ፣ ውብሸት ክፍሌ፣ ቴውድሮስ ታፈሰ፣ ዘላለም አባተ እና በፀጋዬ ብርሀኑ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ፌደራል ዋና ዳኛ መስፍን ባስጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ከሚከተሉት የጨዋታ መንገድ አንፃር ቶሎ ቶሎ በማጥቃት ሽግግር የግብ ዕድሎችን እየፈጠሩ ጨዋታውን ከፍ ወደ አለ ግለት ይቀይሩታል ቢባልም የሆነው በተቃራኒ ነው።
በድንገት ባልተደራጀ እንቅስቃሴ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በሚጣሉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረቶች በሁለቱም በኩል ስኬታማ ሳይሆን አጋማሹ ተጋምሷል።
ሆኖም ግን የጦና ንቦቹ ተሻጋሪ እና የመልሶ ማጥቃት ኳሶች ላይ ትኩረት በመስጠት በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመድረስ ብልጫ ቢኖራቸውም ከግራ መስመር የተሻገረለትን መሳይ ሰለሞን በግንባሩ ገጭቶ ግብጠባቂው ሞይስ በቀላሉ የያዘው እና ጸጋዬ ብርሀኑ ከተሻጋሪ ኳስ ብቻውን ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ በተከላካዮች የተደረበበት አደጋ ለመፍጠር የተቃረቡበት ሙከራዎች ነበሩ።
34ኛው ደቂቃ ላይም በወላይታ ድቻ በኩል ከግራ መስመር ፍፁም ግርማ አሻግሮለት መሳይ ሰለሞን በግቡ ፊት ለፊት በግንባሩ የመታውን ግብ ጠባቂው ሞይስ ከያዘበት በኋላ ሌላ አጋጠሚ አልፈጠሩም። በአንፃሩ በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በዝተው በመከላከል አደረጃጀት ላይ ትኩረት አድርገው ያረፈዱት ስሑል ሽረዎች በተወሰነ መልኩ ዕረፍት መውጫ አካባቢ ወደ ፊት ቢሄዱም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም ለማድረግ ተቸግረው አጋማሹ ግብ ሳይስተናገድበት 0-0 ተጠናቋል።
ጨዋታው ከመልበሻ ክፍል እንደተመለሰ በሰከንድ ውስጥ የጦና ንቦቹ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር በጥሩ መንገድ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ የላከውን ተከላካዮችን አሸንፎ ቴዎድሮስ ታፈሰ የመታውን ግብጠባቂው ሞይስ ለማዳን የተፋውን ኳስ ብዙዓየሁ መቶት ተከላካዮች እንደምንም ያወጡት ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
በ52ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሽረ አላዛር ሽመልስ ከቀኝ ወደ ግራ ኳሱን እየገፋ ቆርጦ በመግባት በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ቢንያም እንደምንም ያዳነበት በጨዋታው የፈጠሩት ወርቃማ ዕድል ነበር። ከእነዚህ ሙከራዎች በኋላ የተነቃቁት ስሑል ሽረዎች 65ኛው ደቂቃ በጨዋታው ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በአጋማሹ ዝውውር ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ጥሩ እንቅስቃቃቄ እያደረገ የሚገኘው አብዲ ዋበላ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ አምልጦ በመግባት የመታውን ግብጠባቂው ቢንያም የመለሰበትን ብርሃኑ አዳሙ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ አሳርፎታል።
ከአራት ደቂቃ በኋላ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ጎል አግኝተዋል። መሳይ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የላከውን ጸጋዬ ብርሀኑ በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ጨዋታውን ወደ አቻነት ከተቀየረ በኋላ ወደ ጥሩ ፉክክር ቢያመራም የተለየ ነገር ሳይኖር ቀጥሎ በመጨረሻው ደቂቃ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሽረዎች በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ የገባው መሀመድ አብዱልለጢፍ በሜዳው ግራ መስመር ያሻገረውን አብዲ ዋበላ ጥሩ ኳስ አግኝቶ አሸማቆ የመታው ኳስ ወደ ሰማይ የሰደዳት ለስሑል ሽረዎች የምታስቆጭ አጋጣሚ ሆና ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።