ሁለቱን አንጋፋ የሸገር ክለቦች የሚያፋልመው ጨዋታ ረፋድ ላይ ይካሄዳል።
በሰላሣ ሁለት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ዙር ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ወደ አደጋው ክልል እንዲጠጉ አድርጓቸዋል፤ በባህር ዳር ከተማ ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም በነገው ጨዋታ ድል ማድረግም በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።
ኤሌክትሪኮች እስከ መጀመርያው ዙር የመጨረሻ መርሐ-ግብሮች ለክፉ የማይሰጥ የመከላከል አደረጃጀት ነበራቸው፤ በሁለተኛው ዙር ግን የቀደመ ጥንካሬያቸው ማስቀጠል መቸገራቸው ተከትሎ የቡድኑን ውጤት እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል። ቡድኑ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች አስር ግቦች ማስተናገዱ እንዲሁም በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱም ስለመከላከል አደረጃጀቱ አሁናዊ ብቃት የሚነግረን ነገር አለ።
ሌላው የቡድኑ ድክመት የግብ ማስቆጠር ችግር ሲሆን በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎችም በአምስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ወጥቷል። ከአቀራረብ አንፃር ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥሩን ለመያዝ መሞከራቸው አይቀሬ መሆኑ ተከትሎ ቡድኑ በተለመደው አቀራረቡ በፈጣን ሽግግር ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደርጋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰራቸው የቅብብል እና የውሳኔ ስህተቶች ካላረመ ግን ዋጋ ሊያስከፍሉት ይችላሉ።
በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቅርብ ሳምንታት አካሄዳቸውን ማስተካከላቸውን ተከትሎ ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ብለው እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል።
ከስምንት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል ያደረጉት ፈረሰኞቹ በእንቅስቃሴ ረገድ አሁንም የሚቀራቸው ነገር ቢኖርም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያሳዩት የሚታይ መሻሻል እንዲሁም በብዙ ረገድ ከተዳከሙበት ወቅት አገግመው የአሸናፊነት መንፈሱ ዳግም ማግኘታቸው በአወንታነቱ የሚነሳላቸው ነጥብ ነው። በተለይም ከሁለት ተከታታይ ድሉ በፊት በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ የግብ ዕድሎችን በመፈፀም ረገድ ጉልህ መሻሻል አሳይቷል። የተጠቀሰው ጥንካሬ ማስቀጠልም ከቡድኑ የሚጠበቅ ትልቁ የቤት ስራ ሲሆን በነገው ዕለትም ባለፉት ሁለት መርሐ-ግብሮች ከገጠማቸው ከፍተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ወልዋሎ እና መቐለ በአንፃራዊነት የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ ጥንካሬውን ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።
ኢትዮ ኤሌክትኮች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬን በቅጣት አያሰልፉም። ለወራት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዮ ሻይዱ ሙስጠፋ ጨምሮ የተቀሩት የፈረሰኞቹ ስብስብ ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች 41 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 70 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 29 አስቆጥሯል።