ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የሽንፈትና አቻ ውጤቶች ያስመዘገቡ ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ከረዷቸዋው የሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ስድስት ጨዋታዎች በኋላ አወንታዊ ውጤቶች አላስመዘገቡም፤ በ26 ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት በመጨረሻው ሳምንት ደግሞ ከመቻል ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎም የዋንጫ ፉክክሩን የሚቀላቀሉበት ዕድል አባክነዋል። በሰላሣ ስድስት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ እርግጥ በሁለቱ ጨዋታዎች የገጠማቸው ቡድኖች በሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ የተሻሻሉና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ያሉ ቢሆንም በጨዋታዎቹ
የነበረው እንቅስቃሴ ቀንሶ ታይቷል። ይህንን ተከትሎ በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሎ ከሚገመተው በሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ቡድን የሚገጥምበት ጨዋታ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ ድል ማድረግ ያስፈልገዋል።
በተለይም የማጥቃት አጨዋወቱ ብቃት መመለስ ትልቁ የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የቤት ስራ ነው። በርግጥ በነገው ጨዋታ በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቡድን እንደመግጠማቸው ከባድ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም በተጋጣሚ የግብ ክልል የሚስተዋለው የስልነት ድክመት መቀረፍ የሚገባው ችግር ነው።
በአስራ ሁለት ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች አካሄዳቸውን ሳያስተካክሉ የውድድር ዓመቱ የዘጠኝ መርሐ-ግብሮች ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ቡድኑ በ17ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ስሑል ሽረ በሰባት ነጥብ፤ በአሁናዊ የደረጃ ሰንጠረዥ የመትረፍ ዕድል ካለው 14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በአስራ ሰባት ነጥብ ርቀት ላይ መገኘቱን ተከትሎ በሊጉ የመትረፍ ዕድሉ እጅግ መንምኗል። በሁለተኛው ዙር ማግኘት ከሚገባው ሀያ አራት ነጥብ ውስጥ አምስቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ባለፉት አምስት መርሐ-ግብሮች በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ በማስቆጠር በውድድር ዓመቱ ከነበረው የማጥቃት አቅም መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ቢችልም ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ መቸገሩ ጉዞውን አክብዶታል።
አሰልጣኝ አታኽልቲ በርሀ በቀጣይ ጨዋታዎች ሰላሣ ሦስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ማስተካከል እንዲሁም አንፃራዊ መሻሻል ያሳየው የፊት መስመሩ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል አምበሉ ፈቱዲን ጀማል አሁንም ከጉዳቱ ያላገገመ በመሆኑ ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በወልዋሎ በኩልም በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግደው ከሜዳ የወጡት ናትናኤል ዘለቀ እና ቡልቻ ሹራ በጉዳት ዮናስ ገረመው ደግሞ በቤተሰብ ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱም ቡድኖች በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።