መቐለ 70 እንደርታ ከአሰልጣኙ ጋር ተለያየ

መቐለ 70 እንደርታ ከአሰልጣኙ ጋር ተለያየ

በፕሪምየር ሊጉ ላይ ውጤት ከራቃቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ ከአሰልጣኙ ጋር መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ ካነሱ ቡድኖች መካከል የ2011 የሊጉ ሻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታ ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከተመለሱ ሦስት የትግራይ ክልል ክለቦች አንዱ ሲሆን በያዝነው ዓመት እያደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች በ29 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን ቡድኑም ትላንት ከአዳማ ከተማ ጋር ካደረገው እና ያለ ጎል ካጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ከዋና አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር እንደተለያዩ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

ከትላንትናው ጨዋታ መቋጫ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በጨዋታው ደስተኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ቆይታ ያላደረጉት የቀድሞው የጉና ንግድ እና አዳማ ከተማ ተጫዋች በአሰልጣኝነት ደግሞ በአክሱም ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ስሑል ሽረ እንዲሁም በመቻል የረዳት አሰልጣኝ ሚናን ተላብሰው የሰሩት አሰልጣኙ ዛሬ ቡድኑ ረፋዱን ባደረገው መደበኛ ልምምድ ላይ መገኘት ያልቻሉ ሲሆን ዝግጅት ክፍላችን ባደረገችው ማጣራት የአሰልጣኙ እና የቡድኑ ቆይታ እንዳበቃለት ሰምተናል።