ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ሐይቆቹ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚፋለሙበት በቀጠናው ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከሽንፈት ከራቁባቸው አራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አስተናግደው ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር በሚያደርጉት ትልቅ ትርጉም ያለው ወሳኝ ጨዋታ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻለ አንድ ደረጃ የማሻሻል ዕድል ያለው ቡድኑ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በፊትም ሆነ በኋላ መስመሩ የተስተዋሉ ድክመቶች ማረም ይኖርበታል። ብርቱካናማዎቹ ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በፊት በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስቆጥረው በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት አለመቻላቸው እንዲሁም በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ካስተናገዱት የግብ መጠን የሚልቅ በሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ማስተናገዳቸው በተጠቀሱት የፊት እና የኋላ ክፍሎቻቸው መጠነኛ መዳከም እንዳለ ጠቋሚ ነው። በነገው ዕለትም በወቅታዊ የማጥቃት አቅም ሲታይ በጥሩ ብቃት ከሚገኘው በፈጣን ተጫዋቾች ከተገነባው የሐይቆቹ የፊት መስመር ለመፋለም ከመቼው ጊዜ በተሻለ አደረጃጀት ወደ ጨዋታው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በሀያ ስምንት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሐይቆቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እያደረጉት ያለውን ጉዞ ለማሳለጥ በአንድ ነጥብ ልቆ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ለመውሰድ ይፋለማሉ።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን ከቀጠሩ በኋላ በብዙ ረገድ የተሻሻሉት ሐይቆቹ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ድል፣ አራት አቻ እና አንድ ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን በወሳኝ ወቅት ላይ ያሳዩት መነቃቃትም ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ አድርሷቸዋል። በነገው ዕለት ድል ካደረገ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል ያለው ቡድኑ ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን ከማሳካቱም በላይ ውጤቶቹ ጠንካራ ቡድኖች በገጠመባቸው መርሐ-ግብሮች ላይ የተገኙ መሆናቸው ደግሞ ቡድኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት እንዳለ ማሳያ ነው። ቡድኑን ከተረከቡ ወዲህ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንዲሁም ቀጥተኛ አጨዋወት ላይ ትኩረት ያደረገ አቀራረብ ያላቸው አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት በነገው ዕለትም በተመሳሳይ አጨዋወት ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የተጋጣሚያቸው የኋላ ክፍል ካለው ወቅታዊ ድክመት አንፃር በነገው ዕለት አጨዋወቱ ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታዎች የሚያገኙበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው መሐመድኑር ናስር በጉዳት አቡበከር ሻሚል ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። በሀዋሳ ከተማ በኩል እግድ ላይ ያለው ኢስራኤል እሸቱ ጨምሮ ቢኒያም በላይ አምስት ቢጫ በቅጣት   ምክንያት የነገው ጨዋታ ሲያመልጠው ሌሎች የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 25 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች 9፤ ድሬዳዋ ከተማዎች 7 ድል አስመዝግበው በ9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀይቆቹ 28 ግቦች ስያስቆጥሩ ብርቱካናማዎቹ ደግሞ 22 ግቦች ከመረብ አገናኝተዋል።