ከ31ኛ እስከ 36ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት ስታዲየም የት እንደሆነ ሲታወቅ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሚያገኙ ጨዋታዎችም የቶቹ እንደሆኑ ፍንጭ ተገኝቷል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚደረገው የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር 29ኛ ሳምንት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከቀጣይ የጨዋታ ሳምንት በኋላም የሀዋሳ ከተማ ቆይታውን እንደሚያጠናቅቅ ይታወቃል። የሊጉ የበላይ አካል ከ31ኛ እስከ 36ኛ ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ወይም በአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሊደረጉ እንደሚችሉ ቀደም ብሎ መርሐ-ግብር አውጥቶ የነበረ ሲሆን አሁን የሊጉ የማሳረጊያ ጨዋታዎች የት ሊደረጉ እንደሆነ ይፋ ሆኗል።
የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎችን ለማከናወን ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ፍላጎት እንዳሳዩ የደረሰን መረጃ ቢያመላክትም አክሲዮን ማኅበሩ ቀድሞ ባወጣው መርሐ-ግብር መሠረት በመመራት ጨዋታዎቹን አዳማ ከተማ ላይ በዩኒቨርስቲው ስታዲየም ለማከናወን መወሰኑን አውቀናል። በተለያዩ ምክንያቶች ሊጉ አዲስ አበባ ላይ መምጣት አለመቻሉ አክሲዮን ማኅበሩ ቀድሞ ያሰበውን የአዳማ አማራጭ እንዲያይ እንዳደረገም ተመላክቷል።
ከሊጉ ጋር በተያያዘ መረጃ የሊጉ የቀጥታ ስርጭት ባለመብት ሱፐር ስፖርት ምናልባት ከ33ኛ ሳምንት ጀምሮ ጨዋታዎችን በቀጥታ ሊያስተላለፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን እየተሰማ ይገኛል።