በበርካታ ደጋፊዎች ታጅበው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
ምሽት 12:00 ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት የተጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን ከ ሲዳማ ቡና አገናኝቷል። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪኮች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ከተረቱበት አሰላለፍ ሽመክት ጉግሳ እና ሀብታሙ ሸዋለምን በማሳረፍ በምትካቸው አንዋር በድሩ እና አበባየሁ ዮሐንስን ሲያስገቡ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናዎች ከመቻል ጋር ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሬድዋን ናስር፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና መስፍን ታፈሰን በማሳረፍ በምትካቸው በዛብህ መለዮ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
በመጀመሪያ ደቂቃ ሙከራ ታጅቦ የተጀመረው ይህ ጨዋታ 1ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ማይክል ኪፕሩቪ ከርቀት በመሆን የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶታል ያንን የተመለሰ ኳስ ለግቡ በቅርበት ላይ በመሆን በጥሩ አቋቋም ላይ የቆመው ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም የግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን ታድጓታል።
በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን መሬት ለመሬት አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ብዙም በማጥቃቱ ረገድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ብዙም ሲደርሱ ያልተመለከትናቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከሜዳው የግራ ክፍል መነሻውን ያደረገውን ኳስ ሄኖክ ገብረህይወት በረጅም ኳስ ከተከላካይ ጀረባ ያቀበለውን ኳስ አቤል ሀብታሙ በፍጥነት ኳስን ይዞ በመግባት ግብ በማስቆጠር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታ እና በኳስ እንቅስቃሴ የተሻሉ ነበሩ። ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ 57ኛው ደቂቃ ላይ የተጋጣሚን ኳስ በመንጠቅ ከሳጥን ውጭ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ ኦጎዶጆ መልሶበታል። እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 62ኛው ደቂቃ ላይ በእዮብ ገ/ማርያም አማካኝነት ከሳጥን ውጭ ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ሲዳማ ቡናዎች በሀብታሙ ታደሰ የግንባር ኳስ እና በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል ደግሞ በናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ኳስ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሁለት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተገኙ የሲዳማ ደጋፊዎችን በደስታ ያደበላለቀ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ሲዳማዎች በተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው ተጋድሎ የሚመለሱትን ኳሶች ደጋግመው የሞከሩ ሲሆን ከዛ ሁሉ እልህ አስጨራሽ ትግል ሙከራ በኋላ ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ይህንንም ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች በይገዙ ቦጋለ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ታግዘው ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።