ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ፋሲል ከነማ ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች መልስ ድል ለማድረግ መሪው መድን ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ዘጠኝ ከፍ ለማድረግ የሚፋለሙበት ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ ነው።

በሰላሣ አምስት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠት ፋሲል ከነማዎች ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል አድርገው ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመሻገር የሊጉን መሪ ይገጥማሉ።

ዐፄዎቹ ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ አልቻሉም፤ ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም በአጠቃላይ ያለፉት ጨዋታዎች ውጤቶቹ ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ እንዳይል አድርጎታል።
ለዚህ እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ የቡድኑ የግብ ማስቆጠር አቅም መዳከም ነው።

መቻል፣ ወልዋሎ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በገጠመባቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ብቃት የነበረው የማጥቃት ክፍል ውጤታማነቱ እየቀነሰ መምጣቱም በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ጨዋታዎች ለማሸነፍ ፈታኝ እንዲሆንበት አድርጎታል። የቀደመ ጥሩ የአፈፃፀም ብቃቱ ለማስቀጠል ተቸግሮ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወት ድክመት መቅረፍ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ቡድኑ ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ በዘለለ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የሚፈጥርበት ሁኔታ ማመቻቸትም ትልቁ የቤት ስራው መሆን ይገባዋል።

በሀምሳ አራት ነጥቦች በመሪነቱ ላይ የተሰየሙት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻው ሳምንት በባህርዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ድል አስመዝግበው ከተከታያቸው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነቱን ወደ ዘጠኝ ከፍ ለማድረግ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

በወላይታ ድቻ ሽንፈት ካስተናገዱበት የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ በኋላ በተከናወኑ ሰባት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አንድ ነጥቦች አስራ ዘጠኙን በማሳካት በወጥነት የዘለቁት መድኖች በመጨረሻው ጨዋታ ሽንፈት ብያስተናግዱም አሁንም በስድስት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰው የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋትና በመሪነቱ ለመደላደል በመጨረሻው ጨዋታ የተስተዋሉባቸው ድክመቶች ማረም መቻል አለባቸው፤ ቡድኑ ሳቢ እና ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የውድድር ዓመቱ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ቀድሞ ግብ በማስቆጠር መምራት ቢጀምርም መሪ የሆነበትን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ጨዋታውን የተቆጣጠረበት መንገድ ግን መሻሻል የሚገባው ነው። ለወትሮ ለኳስ ቁጥጥር ቅድምያ በመስጠት እንዲሁም በመከላከል ጥንካሬው የሚታወቀው መድን ከተጠቀሰው ቅፅበት በኋላ በአመዛዡ ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል ሁኔታ ወደ መከላከሉ ለማዘንበል መወሰኑ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ የመከላከል ሂደቶች ስህተት መፍጠሩ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት የድሕረ ጨዋታ አስተያየት ቡድናቸው ‘ታክቲካሊ’ ጥሩ እንዳልነበረ እና የመከላከል ድክመቶች መኖራቸው የጠቀሱት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በነገው ጨዋታ በተከላካይ  ክፍሉ ላይ የተስተዋሉ ድክመቶች መቅረፍ እንዲሁም በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች አስቆጥሮ በጨዋታው የቀደመ ጥንካሬውን ማስቀጠል ያልቻለውን የፊት መስመር ጥምረት ማስተካከል ይኖርባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ባላቸው ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ እንዲሁም ያሉበት የፉክክር ደረጃ የተለያየ ቢሆንም በሁለቱ ቡድኖች ባለው ነጥብ ፈላጊነት ምክንያት ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በፋሲል በኩል አቤል እንዳለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን የእዮብ ማቲያስ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ሀብታሙ ተከስተ በበኩሉ ከጉዳት ተመልሷል። በረከት ግዛው ግን በቅጣት ምክንያት ነገ ቡድኑን አያገለግልም።በኢትዮጵያ መድን በኩል ከሚልዮን ሰለሞን ውጭ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።

ቡድኖቹ በሊጉ 6 ጊዜ ሲገናኙ ፋሲል ከነማ 2 ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 1 ጨዋታ ላይ ድል ሲቀናቸው 3 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። መድን 2 ጎል ሲያስቆጥር ፋሲል 4 ጎል ማስቆጠር ችሏል።