ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ነብሮቹ እና ቢጫዎቹ የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ 3ኛ መርሐ-ግብር ነው።

በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ወልዋሎ በሚገኝሙበት ጨዋታ ድል ማስመዝገብ ብያንስ ሁለት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።

በሁለተኛው ዙር በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ደረጃ ሲታይ የወጥነት ችግር የሚስተዋልባቸው ነብሮቹ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች ማስመዝገብ የቻሉት ድል አንድ ብቻ ነው። ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ ሁለት ሽንፈት፣ አንድ ድል እና አምስት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ አባዜው የቀጠለው ቡድኑ በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች ለክፉ የሚሰጥ ብቃት ባያሳይም የወጥነት እና የግብ ማስቆጠር ችግሮቹ ግን ዋነኛ ድክመቶቹ ናቸው። በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች በሁለቱም አጋማሾች በተመሳሳይ ብቃት የመጫወት ድክመት የነበረባቸው ነብሮቹ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታም ተመሳሳይ ነገር ተስተውሏል። ቡድኑ በጨዋታው ከመጀመርያው አጋማሽ ይልቅ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ቢንቀሳቀስም በእርጋታ ማጣት እና በውሳኔ አሰጣጥ ችግሮች ምክንያት የተገኙት ዕድሎች መጠቀም ባለመቻሉም ለሽንፈት ተዳርጓል። ይህንን ተከትሎም የተጠቀሰው የወጥነት ችግር፣ በግብ ፊት የሚስተዋሉ የውሳኔ አሰጣጥ ችግሮች እንዲሁም ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀት ማስተካከል የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የቤት ስራዎች ናቸው።

በአስራ ሦስት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከረፈደም ቢሆን መጠነሻ መሻሻል አሳይተዋል። በመጨረሻው መርሐ-ግብር በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ የተጋሩት ቢጫዎቹ በቅርብ ሳምንታት ያሳዩት መሻሻል ከቀድሞ የተሻለ ቅድመ ግምት እንዲሰጣቸው ያስገድዳል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት ማስተናገዱ እንዲሁም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር መቻሉ ከቀድሞ ብቃቱ አንፃር ሲታይ መሻሻል እንዳሳየ አመላካች ቢሆንም በ14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው እና በወቅታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ በሊጉ ተራፊ ከሚሆነው ድሬዳዋ ከተማ በአስራ ስድስት ነጥቦች መራቁ በሊጉ የመትረፍ ዕድሉ እጅግ ተመናምኗል። ወልዋሎዎች፡ በሊጉ ለመቆየት ያላቸው ዕድል ጠባብ ቢሆንም እስከ መጨረሻው ድረስ ለመፋለም ግን በ16ኛው ሳምንት በነገው ተጋጣሚያቸው ሀድያ ሆሳዕና ያሳኩት የውድድር ዓመቱ ብቸኛ ድል ለመድገም ወቅታዊ የማጥቃት ብቃታቸው ማስቀጠል እንዲሁም የሚስተዋሉ የመከላከል ድክመቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል። 

በነብሮቹ በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት መለሰ ሚሻሞ እና ጫላ ተሽታ በተጨማሪ ሰመረ ሀፍታይ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ተከላካዩ ዳግም ንጉሴ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ አይሳተፍም፤ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ሆነው የሚቀርቡ ይሆናል። በወልዋሎ በኩል ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፉት ቡልቻ ሹራ እና ናትናኤል ዘለቀ ማገገም ባለመቻላቸው ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አማካዩ ሀብታሙ ንጉሴም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆኗል። በመጨረሻው ጨዋታ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ያልተሰለፈው ዮናስ ገረመው ግን ቡድኑን ተቀላቅሎ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

የተሰረዘው እና በሀድያ ሆሳዕና አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር አንድ ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ዘንድሮ ያደረጉት ጨዋታ በወልዋሎ የአንድ ለባዶ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።