ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ያጠናከረበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ያጠናከረበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ በመድን 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ በ28ኛው ሳምንት ከስሑል ሽረ ጋር 1ለ1 ከተለያየበት ቋሚ አሰላለፍ የአምስት ተጫዋች ለውጥ አድርገው ዮናታን ፍሰሃ ፣ቢኒያም ላንቃሞ፣ አቤል እንዳለ፣ በረከት ግዛው እና ማርቲን ኪዛን አሳርፈው  በምትካቸው ኢዮብ ማቲያስ፣ብሩክ አማኑኤል፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ዳግም አወቀ እና ቢኒያም ጌታቸውን ይዘው ሲገቡ ኢትዮጵያ መድን በበኩላቸው ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱበት ከመጀመሪያው ቋሚያቸው  አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ  አዲስ ተስፋዬን በአለን ካይዋ ተክተው ቀርበዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ መጀመሪያ ፊሽካ ጅማሮውን ያደረገው ተጠባቂው የረፋዱ ጨዋታ አስር ደቂቃዎች እስኪቆጠሩበት ድረስ ምንም አይነት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ባያስመለክተንም ኢትዮጵያ መድን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደፊት በመሄድ ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። አፄዎቹ  በአንፃራዊነት አልፈው አልፈው ኳስ ይዘው ለመጫወት ቢጥሩም ተረጋግተው መጫወት ያልቻሉበትን የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች አስመልክተውናል።

ጨዋታው በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ይዘው ተረጋግተው መጫወትን ምርጫቸውን አድርገው አጋማሹ አካፋይ ላይ ቢደርሱም ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። ይልቁንስ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት አድርገው የኳስ ብልጫ ለመውሰድ ሲጥሩ አስተውለናል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ፍፁም ርቀት ላይ ሆኖ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ የግቡ ዘብ አቡበከር ኑራ በቀላሉ የተቆጠጣረበት ሙከራ ሲጠቀስ 34ኛው ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ የዘው ገብተው ኪሩቤል ዳኜ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አታሎ ለማለፍ ሲጥር ተጎድቻለሁ ብሎ ወድቆ ሳይጠቀም ቀርቶ በማስመሰል ወድቀሃል በሚል ቢጫ ካርድ የተመለከተበት ክስተት የአፄዎቹ አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ ነበር።

ወደ ፊት እየሄዱ ጫና እያሳደሩ የሰነበቱት መድኖች የመሪነት ግብ ለማስቆጠር 42 ደቂቃዎችን ጠብቀው በአጋማሹ መገባደጃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በ43ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረሥላሴ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ ደርሶ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ አለን ካይዋ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮ መድኖች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አስችሏቸዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ፋሲል ከተማዎች ጠንከር ብሎ ተመልሰው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል መድረስ ችለዋል። ሆኖም ግን ሳይጠበቅ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ በአፄዎች ተከላካይ መነሻነት የተገኘውን ኳስ አቡበከር ሳኒ አሻግሮት  አለን ካይዋ መረብ ላይ አሳርፎ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

ከሁለተኛ ግቧ በኋላ ፋሲሎች የተወሰኑ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የፊት መስመራቸውን አጠናክረው ጫና ለማሳደር ቢጥሩም የመድኖች የኋላ መስመር እንዳሰቡት ሊሆንላቸው አልቻለም፤ እንዲሁም የሚያደርጉት ሙከራ ጠንካራ ሳይሆንላቸው ቀርቶ በቀላሉ ሲመለስባቸው ተመልክተናል። ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በረጃጅም ኳሶች ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለው ሙከራዎችን አድርገዋል። በ76ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ አለን ካይዋ አግኝቶ በቀላሉ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ በዮሐንስ ደርሶ ቅልጥፍና የተመለሰባቸው ኳስ ጨዋታውን ወደ መጨረስ የቀረበ አስቆጪው አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ወደ መገባደጃ ሲቃረብ የአፄዎቹ ጫና በርትቶ ቢያንስ ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ግብ ለማግኘት በሙሉ ሀይላቸው ተጠቅመው በማጥቃቱ ተጠምደው የመድኖችን የኋላ መስመር መፈተን የቻሉበትን ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህ 82ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ አሚር ሙደሰር ጠንከር አድርጎ መጥቶ አቡበከር ኑራ አግዶበታል። በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ሜዳ የገባው ጃቢር ሙሉ ከሳጥን ውጪ ሆኖ የመታውን ኳስ የግቡ ዘብ ያገደበት እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ ላይ ማርቲን ኪዛ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግሩም እንቅስቃሴ ያስመለከተው አቡበከር ኑራ ያወጣባቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

አፄዎቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫናዎችን ማሳደር ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ኢትዮጵያ መድንም ተጨማሪ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል ፤በተለይም 84ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ መድኖች ያደረጉት ሙከራ ሲታወስ ዳዊት ተፈራ የአፄዎቹ ግብ ጠባቂ ወደ ውጪ መውጣቱን በሚገባ ተመልክቶ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ የጣለውን ኳስ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ቅፅበት ይጠቀስ እንጂ ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ለመድኖች ሦስት ነጥብ ከሁለት ግብ ጋር በማጎናፀፍ ፍፃሜውን አግኝቷል።