ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ባህር ዳር ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ባህር ዳር ከተማ

ሀምራዊ ለባሾቹ ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት የጣና ሞገዶቹ ደግሞ ከመሪው ጋር ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስን አንድ ለባዶ ካሸነፉ በኋላ በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት በሰላሣ ሰባት ነጥቦች  9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል ማድረግ ቢያንስ ሁለት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።

ከ17ኛ እስከ 25ኛ ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው ውጤቶች የውድድር ዓመቱ ጉዟቸው ያቃኑት ሀምራዊ ለባሾቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር መራራቃቸውን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ የሚጠጉበትን ዕድል አባክነዋል።

ንግድ ባንክ በመጨረሻዎቹ  ሁለት መርሐግብሮች ጨምሮ በውድድር ዓመቱ አስር የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል፤ ይህም በአስራ ሁለት እና አስራ አንድ ጨዋታዎች አቻ ከተለያዩት ሦስት ክለቦች ቀጥሎ በርከት ያለ የአቻ ውጤት ያስመዘገበ ያደርገዋል። ማሸነፍ የሚችለውን ጨዋታ ላይ በጥቃቅን ስህተቶች ነጥብ መጣልም የቡድኑ ድክመት ሲሆን በሊጉ ግርጌ ከተቀመጠው ወልዋሎ ባደረጉት የመጨረሻ የሊጉ መርሐግብር ላይ የተስተዋለውም ይህ ነው። ይህንን ተከትሎ የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድን ከዚህ ቀደም ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ የነበረውን ጨዋታን የመቆጣጠር ክህሎት መመለስ የሚኖርበት ሲሆን በነገው ዕለትም ስምንት ግቦች አስቆጥሮ ሦስት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበ በጠንካራ ወቅታዊ ብቃት የሚገኝ ቡድን ስለሚገጥም የመከላከል አደረጃጀቱን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል።

በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች መሪውን ካሸነፉበት ጣፋጭ ድል መልስ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል።

ከዚህ ቀደም በጠጣሩ የመከላከል አደረጃጀት እንዲሁም ወጥነት ባልነበረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የሚታወቀው የጣና ሞገዶቹ ስብስብ በቅርብ ሳምንታት የወጥነት ችግሩ ቀርፎ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቷል። በተለይም ደግሞ
ከዚ ቀደም በአፈፃፀም ችግሩ ሲታማ የነበረው
የቡድኑ የማጥቃት ጥምረት ጉልህ ስህተቶች እየቀነሰ መምጣቱ እና በርከት ያሉ ግቦች ማስቆጠር መጀመሩ ቡድኑን አጠናክሮታል። የማጥቃት ክፍሉ ከተከታታይ ድሎቹ በፊት በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐግብሮች ስምንት ግቦች ማስቆጠሩም የመሻሻሉ ማሳያ ነው። የነገው ጨዋታም ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት እና ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ዝቅ የሚያደርጉበት ዕድል ስለሚሰጣቸው ወሳኝነቱ ትልቅ ነው፤ ስለዚ ባለፉት ጨዋታዎች የታየው የሜዳ ላይ ብቃት እና የማሸነፍ መንፈስ ማስቀጠል ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን የሚጠበቅ ነው።

በጣና ሞገዶቹ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ባሲሩ ኦማር እና ፈቱዲን ጀማል በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም። የሱሌይማን ሀሚድ እና የእንዳለ ዮሐንስ መሰለፉም አጠራጣሪ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ካሌብ አማንኩዋህ እና ተመስገን ተስፋዬ ደግሞ በቅጣት የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ክለቦቹ በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታዎች ድል ሲያደርጉ የተቀረው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።