ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ደጋፊዎች የታደሙበት የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ የማይክል ኪፕሩቭል ብቸኛ ጎል ሲዳማን ባለ ድል አድርጎል።
ሲዳማ ቡና ጣፋጭ ድል አሳክተው ከተመለሱበት የባለፈው አስተላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጊት ጋትኩት፣ አበባየሁ ሀጂሶ፣ በዛብህ መለዮ እና ሳሙኤል ሳሊሶ አሳርፎ ሬድዋን ናስር፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ አስቻለው ሙሴ እና
መስፍን ታፈሰ ተክቶ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከሽንፈት ከመጣው የባለፈው ስብስባቸው ወላይታ ድቻዎች የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ናትናኤል ናሴሮ፣ ቴውድሮስ ታፈሰ እና ያሬድ ደርዛ አስቀምጠው ኬኔዲ ከበደ፣ አብነት ደምሴ እና መሳይ ሰለሞን ተክተው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።
ፌደራል ዳኛ ሃይማኖት አዳነ ሲያስጀምሩት የሁለቱን ጨዋታ ለመከታተል ቁጥሩ በርካታ የሆነ ተመልካች በስታዲየሙ ታድሞ ነበር።
ከጅማሮ አንስቶ ህይወት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል የተመለከትነው ገና በአምስተኛው ደቂቃ ነበር። ወደ ራሱ ሜዳ ተጠግቶ የነበረው አጥቂው ሀብታሙ ታደሰ በጥሩ ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን አፈትልኮ የገባው ማይክል ኪፖሩቭል ኳሱን እንዳይቆጣጠር የግብ ክልሉን ለቆ የወጣውን ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱን አሸንፎ ማይክል እጅግ ድንቅ በሆነ መንገድ መጥኖ የላካት ኳስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የጀመሩት የጦና ንቦቹ 9ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ውብሸት የላከለትን ካርሎስ ዳምጠው ኳሱን በግንባሩ ጨርፎ ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ ይዞበታል። ሲዳማ ቡናዎች ኳስ ሲያጡ በቁጥር በዝተው እየተከላከሉ በፈጣን ሽግርር ለደጋ ለመፍጠር ከመሞከር ውጭ ወላይታ ድቻዎች ኳስ ይዘው ክፍተቶችን በመፈለግ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ብልጫ ወስደው ሲቆዩ በተወሰነ መልኩ ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ለመላክ ቢጥሩም ስኬታማ መሆን አልቻሉም።
የአጋማሹ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎችም ድቻዎችም በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ ይውሰዱ እንጂ ጥቃታቸው እምብዛም ነበር። ይልቁንም 36ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን መስፍን ታፈሰ በግንባሩ በመግጨት አደገኛ ሙከራ ካደረገበት አጋጣሚ ውጭ በአመዛኙ ሙከራዎች ሳንመለከት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በድቻዎች ፈጣን ጥቃት ቢጀምርም በብዙ ልዩነት የሚፈጥር ኢላማቸውን የጠበቀ ሙከራ ሊያደርጉ አልቻሉም። ሲዳማ ቡናዎች እንደመጀመርያው አጋማሽ ድቻዎች ኳሱን እንዲጫወቱ እየፈቀዱ ወደ ራሳቸው ሜዳ ሲመጡ በጠንካራ መከላከል ኳሱን በማራቅ በመልሶ ማጥቃት ጨዋታውን ለመቆጣጠር ቢያስቡም በሙከራ በኩል ስኬታማ አልነበሩም።
74ኛው ደቂቃ ላይ ሳይጠበቅ የተላከለትን ኳስ መሳይ ሰለሞን ኳሱን ወደ ኋላ ገጭቶ የመታውን ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ ንቁ ሆኖ የያዘበት እንዲሁ 82ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ወደ ሳጥን የላከውን ያሬድ ደርዛ ኳሱን ተቆጣጥሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ያዳነበት ወለይታ ድቻዎች ሙከራዎች ነበሩ።
የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በተለይ በጭማሪ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በአመዛኙ ትኩረታቸውን የያዙትን ውጤት አስጠብቀው ለመውጣ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች የአቻነት ጎል ለማስቆጠር በይበልጥ ተጭነው ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች ፈተና የነበሩ ቢሆንም ፈተናውን በተገቢው መንገድ ተወጥተው ሲዳማ ቡናዎች ወሳኝ ድላቸውን 1-0 በማሸነፍ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ደስታቸውን አጣጥመው ወጥተዋል።