ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ እና አዞዎቹ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚፋለሙት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።

ከሦስት ተከታታት ሽንፈቶች መልስ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ብርቱካናማዎቹ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት አልቻሉም። በነገው ዕለትም ካሉበት የፉክክር ደረጃ ውስጥ ከተፎካካሪዎቻቸው ላለመራቅ በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው ጨዋታቸውን ይከውናሉ። 

ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት
ብርቱካናማዎቹ በቅርብ ሳምንታት በቀጠናው የሚገኙ መቐለ እና ኤሌክትሪክ የመሳሰሉ ክለቦች በተመሳሳይ ደካማ ውጤት ማስመዝገባቸው ጠቀማቸው እንጂ ያሉበት ሁኔታ በእንቅስቃሴም ይሁን በውጤት ረገድ አጥጋቢ አይደለም።
በውድድር ዓመቱ የኳስ ቁጥጥርን ዋነኛ የግብ ዕድል መፍጠሪያ መንገዱ አድርጎ የዘለቀው ቡድኑ
በእንደ ከዚህ ቀደም ደረጃ ባይሆንም አሁንም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር ቡድን ነው።
ሆኖም በቅብብሎች ሰብሮ ለመግባት ብዙ ሲቸገር መግባት በቻለባቸው አጋጣሚዎችም መጨረስ እየተሳነው ከኋላ የሚተወው ክፍተትም ለጥቃት ሲያጋልጠው በቅርብ ጨዋታዎች ስንታዘብ ቆይተናል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ስድስት ግቦች ማስተናገዱ እንዲሁም አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም በፊት እና ኃላ ላሉበት ችግር ማሳያ ነው።

የነገ ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማም ምንም እንኳ በቀደመ የማጥቃት ጥንካሬው ባይገኝም ከተከላካይ መስመር ጀርባ በፈጣን ሽግግር ለመግባት የሚያስችል መዋቅር ያለው በመሆኑ የመከላከል አደረጃጀቱ ይበልጥ ማጠናቀር ይኖርበታል።

በሰላሣ አምስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ።

ባለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት አዞዎቹ ሳይታሰብ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ካሉ ክለቦች ጋር ነጥቡ እየተቀራረቡ በመሆኑ በቶሎ ከድል ጋር ተገናኝተው በአስተማማኝ የነጥብ ርቀት ላይ መቀመጥ ያስፈልጋቸዋል።

አዞዎቹ ከድል ጋር ከተራራቁ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ከማስቆጠራቸው በተጨማሪ በመጨረሻ ሦስት መርሐ-ግብሮች ሽንፈት አስተናግደዋል።
ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በተጨማሪ ቡድኑ ባልተረጋጋ የተከላካይ መስመር ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ማስተናገዱ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የቡድኑ ጠንካራ ጎን የነበረው የፊት መስመር ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነው።

እርግጥ የነገ ተጋጣሚው ማጥቃት ላይ ደካማ ሆኖ የከረመ ከመሆኑ አንፃር ይህ የኋላ ክፍል ችግሩ ላይጋለጥ ቢችልም ከስህተት የፀዳ ዘጠና ደቂቃ እንደሚያሳልፍ በእርግጠኝነት መናገር ግን አይቻልም።

ይህንን ተከትሎ የፊት መስመሩ ወደ ቀደመ ብቃቱ የሚመልስ ስራ መስራት እንዲሁም የተከላካይ መስመሩ ማሻሻል ከአሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚጠበቅ ነው።

ድሬዳዋ ከተማዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ከመሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል አሸናፊ ፊዳ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲታወቅ በተጨማሪም በላይ ገዛኸኝ ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ የሚያርቀውን ጉዳት በማስተናገዱ በነገው ጨዋታ አይሳተፍም። ላለፉት ሳምንታት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የሰነበተው በፍቅር ግዛው ግን ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል።

ቡድኖቹ በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 5 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ 4 አሸንፏል ፤ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ 14 ፣ ድሬዳዋ ደግሞ 9 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።