በሊጉ ግርጌ የተቀመጠው ወልዋሎ እና ወደ ወራጅ ቀጠናው የተጠጋው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከድል ጋር ለመታረቅ የሚፋለሙበት ጨዋታ ረፋድ ላይ ይከናወናል።
በአስራ ሦስት ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ ከተካሄደው የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ወልዋሎዎች በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል፤ ቡድኑ ባለፉት የጨዋታ ሳምንታት በውድድር ዓመቱ ካሳየው ብቃት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም ጉልህ የመከላከል ስህተቶቹ ዋጋ እያስከፈሉት ድል ማድረግ አልቻለም። በመጨረሻዎቹ ሰባት መርሐግብሮች ውስጥ በስድስቱ እየመራ ውጤቱን ሸማስጠበቅ ተስኖት ነጥብ ለመጋራት እና ለሽንፈት የተዳረገው ቡድኑ መሰል ድክመቶቹን ለመቅረፍ የመከላከል አደረጃጀቱን ማስተካከል ይኖርበታል። በቢጫዎቹ በኩል የሚነሳው አወንታዊ ጎን በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያሳዩት መሻሻል ነው፤ ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በአንፃሩ በጨዋታዎቹ አምስት ግቦች አስተናግዷል። ይህንን ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ሰላሣ ስምንት ግቦች በማስተናገድ በሊጉ ቀዳሚ የሆነው የተከላካይ ጥምረቱ ማስተካከል የአሰልጣኝ አታኽልቲ በርሐ ቀዳሚው ሥራ መሆን ይገባዋል።
በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሦስት ተከታታት ሽንፈቶች በማገገም ካንዣበበባቸው የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ቢጫዎቹን ይገጥማሉ።
ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ዙር ላይ ወጥ ብቃት ማሳየት ከከበዳቸው ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተካሄዱ አስር ጨዋታዎች ሰባት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ ካጠናቀቀው የመጀመሪያው ዙር የነበረው ውጤታማነት ማስቀጠል ባለመቻሉ ላለመውረድ በሚደረገው ፍልሚያ ሊቀላቀል ችሏል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ በዙሪያው ካሉ ቡድኖች ጋር ተጨማሪ ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። እርግጥ ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ግርጌ የተቀመጠ ቡድን እንደመግጠሙ ከባለፉት ጨዋታዎች አንጻር ሲታይ ቀላል ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም የግብ ዕድሎች ለመፍጠር አዳጋች የሆነበት አቀራረብ ላይ ግን ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል። ከባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ የወጣው ቡድኑ በፊት መስመሩ ማድረግ ከሚገባው ለውጥ በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስተናገደውን የመከላከል አደረጃጀቱን የማጠናከር ሥራ ይጠብቀዋል። ተጋጣሚው ወልዋሎ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረ እንደመሆኑም በመከላከሉ ረገድ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው።
በወልዋሎ በኩል ጉዳት ላይ ከሰነበቱት ቡልቻ ሹራ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሀብታሙ ንጉሤ በተጨማሪ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ሳምሶን ጥላሁን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ 1 ጊዜ ድል ሲቀናው 2 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ወልዋሎ 5 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 3 ግቦች ማስቆጠር ችሏል።