ኢትዮጵያ ቡና መሪውን መድን እግር በእግር ለመከታተል አዳማ ከተማ ደግሞ ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ለመቅረብ የሚያደርጉት ጨዋታ በሰንጠረዡ ላይ እና ታች ባለው ፉክክር ተጠባቂ ነው።
በአርባ ስምንት ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዛሬ ድል በማድረግ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አስራ ሁለት ከፍ ያደረገውን መሪውን መድን እግር በእግር ለመከታተል በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።
በሲዳማ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ሦስት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገቡት ቡናማዎቹ ከአንድ ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን የሚጠበቅ ብቃት በማሳየት እዚህ ደርሰዋል። በተለይም በሁለተኛው ዙር ይበልጥ የተሻሻለው ቡድኑ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ የዛሬውን ሳይጨምር ከመሪው መድን ጋር እኩል ነጥብ ሰብስቧል። በዙሩ ከተከናወኑ አስር ጨዋታዎች ሰባት ድል፣ ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ቡናማዎቹ በጨዋታዎቹ ማግኘት ከሚገባቸው ሰላሣ ነጥቦች ሀያ ሁለቱን በማሳካት ውጤታማ ጉዞ በማድረግ ላይ ቢገኙም በግብ ማስቆጠር ረገድ ያላቸው ጥንካሬ ግን መሻሻል የሚገባው ነው። በተጠቀሱት አስር ጨዋታዎች ድሬዳዋን ሁለት ለባዶ ካሸነፉበት መርሐግብር ውጭ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስመዝገብ ያልቻለው ቡድኑ በቀጣይ በግብ ማስቆጠሩ በኩል ያለበትን ውስንነት መቅረፍ ግድ ይለዋል። በሊጉ ከመሪው መድን ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስተናገዱት ቡናማዎቹ በነገው ዕለት በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም ተጋጣሚያቸው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ እና በሂደት የመከላከል ድክመቱን በማረም ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ በነገው ዕለት ለተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ድክመታቸው መፍትሔ ማበጀት ይኖርባቸዋል።
በሃያ ስድስት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያስመዘገቡትን ድል መድገም በ15ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ እንዲያጠቡ ዕድል ይሰጣቸዋል።
አዳማ ከተማዎች አምስት ግቦች አስተናግደው ከተሸነፉባቸው የ25ኛ እና 26ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች በኃላ በብዙ ረገድ ተሻሻሽለዋል። ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዋች ከሽንፈት መራቁ፤ የከዚህ ቀደም ዋነኛ ድክመቱ የነበረው የመከላከል ድክመት በማረም በሦስቱ መርሐግብሮች አንድ ግብ ማስተናገዱ እንዲሁም በመጨረሻው ሳምንት ዳግም ወደ ድል መንገድ መመለሱም የመሻሻሉ ማሳያዎች ናቸው። በተለይም በ20ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ካሸነፉበት ጨዋታ በኃላ በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች ላይ አስራ አንድ ግቦች ያስተናገደው እና
በሊጉ ከወልዋሎ ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል በቅርብ ሳምንታት የሚታይ ለውጥ በማምጣት የሚቆጠሩበትን ግቦች ቀንሷል።
አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ የቡድኑ ቀንደኛ ችግር የነበረው የኋላ ክፍል በማስተካከል ረገድ በአወንታነቱ የሚጠቀስ ስራ መስራት ቢችሉም በማጥቃቱ በኩል ያላቸው ድክመት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ባለፉት አስር ጨዋታዎች አምስት ግቦች ብቻ ያስቆጥረውና ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ጉልህ ድክመት የሚስተዋልበት የማጥቃት ጥምረቱም ለጠንካራው የቡና ተከላካይ ክፍል ሊፈትን በሚችል አኳኋን መቅረብ ግድ ይለዋል።
የነገው ወሳኝ ጨዋታም ሊጉ ወደ ከተማቸው ከማቅናቱ በፊት የሚደረግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር እንደመሆኑ ብያንስ የነጥብ ልዩነቱን አጥብበው ወደ ከተማቸው ለማቅናት እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር የተሻለ ተስፋ ለመሰነቅ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንፈስ ወደ ጨዋታው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በተከታታይ በተመለከተው የሦስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የማይኖር ሲሆን ረዳት አሰልጣኝ ታፈሠ ተስፋዬ ቡድኑን ይመራል። መላኩ አየለ ፣ እያሱ ፈጠነ እና ወልደአማኑኤል ጌቱ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በአዳማ ከተማ በኩል ከባድ ጉዳት ያጋጠመው አሜ መሐመድ በነገው ጨዋታ የማይኖረው ተጫዋች ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 45 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 23 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 10 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 77 ፤ አዳማ 42 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።