ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሦስት ነጥብ የሚበላለጡ እና ለሳምንታት ከድል ጋር የተራራቁ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ባለው የነጥብ አስፈላጊነት እና ባላቸው የጨዋታ መንገድ ማራኪ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በሰላሣ አምስት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ መሻገርን እያለሙ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ዐፄዎቹ ስምንት ግቦች አስቆጥረው ካሸነፉባቸው ሦስት መርሐግብሮች በኋላ በተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም፤ በሦስቱ ሽንፈት አስተናግደው በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎም ዳግም ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ቀርበዋል። ቡድኑ በወራጅ ቀጠናው ጫፍ ከተቀመጠው ክለብ በአምስት ነጥብ መራቅ መቻሉ እንዲሁም በነገው ዕለት ድል ካደረገ እስከ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል በመያዙ አሁንም ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ዕድሎች ያሉት ቢሆንም ከቀጠናው ሙሉ ለሙሉ ለመላቀቅ እና በቀጣይ መርሐግብሮች ችግር ውስጥ ላለመግባት ግን ከድል ጋር መታረቅ ይኖርበታል።

ፋሲል ከነማ በየጨዋታዎቹ የወጥነት ችግር ቢስተዋልበትም አሁንም የኳስ ቁጥጥር ለመውሰድ የሚታትር ቡድን ነው፤ ሆኖም በተከላካይ ክፍሉ  ላይ የሚስተዋለው ግለ-ሰባዊ እና መዋቅራዊ ስህተት እንዲሁም ከ22ኛው እስከ 24ኛው ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው የማጥቃት ጥምረቱ በመጨረሻዎቹ አምስት መርሐግብሮች አስተዋጽኦው ቀንሶ ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩ በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ፋሲሎች በመድን ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የሊጉ ጠንካራ የመከላካል ጥምረት ያለውን ቡድን አልፈው በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎች መፍጠራቸው በነገው ጨዋታ የተሻለ ነገር እንዲጠበቅባቸው ቢያደርግም በቀጣይ በጨዋታው ሊያንሰራሩ በሚችሉበት ጊዜ የሰሩት እና የጨዋታውን መልክ የቀየረ ስህተት መቅረፍ ግድ ይላቸዋል።

በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለት የደረጃ መሻሻል የሚሰጣቸውን ድል ለማግኘት ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ስድስት ጨዋታዎች አራት ድሎች፣ አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አስራ ሦስቱን ያገኙት ሀምራዊ ለባሾቹ ቀጥለው በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች በውጤታማነቱ መዝለቅ አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ ከመቻል እና ባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረጋቸው ጠንካራ ፉክክር በተደረገባቸው መርሐግብሮች ግብ ሳያስተናግድ አንድ ነጥብ ይዞ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም በውድድር ዓመቱ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በርከት ያሉ ነጥቦችን ጥሏል፤ በሊጉም ከድሬዳዋ ከተማ እና ስሑል ሽረ በመቀጠል ከሌሎች ሁለት ክለቦች ጋር በጣምራ በርከት ያሉ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል።

ባህር ዳር ከተማን በገጠሙበት የመጨረሻው ሳምንት ጠንካራ መርሐግብር ላይ እንደወትሮው ጥሩ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ንግድ ባንኮች በጨዋታው የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ የነበራቸው ብቃት ግን መሻሻል የሚገባው ነው። አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ከተጠባቂው ጨዋታ በፊት በሦስት መርሐግብሮች ስምንት ግቦች አስቆጥሮ ወደ ጨዋታው የቀረበው የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት ክፍል በመግታት ረገድ ውጤታማ ስራ መስራት ቢችሉም በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ከተሻለ የኳስ ቁጥጥር ባሻገር በርከት ያሉ የጠሩ ዕድሎች  በመፍጠር ያለባቸውን ውስንነት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

በፋሲል ከነማ በኩል አቤል እንዳለ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን የአማኑኤል ገብረሚካኤል  መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በረከት ግዛው ግን ከቅጣት ይመለሳል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ተመስገን ተስፋዬ እና ካሌብ አማንክዋህ ከቅጣት ቢመለሱም ብሩክ እንዳለ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ባሲሩ ኡማር አሁንም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው፤ ፈቱዲን ጀማል እና ሱሌማን ሀሚድ ግን ከጉዳታቸው ሙሉ በሙሉ ባያገግሙም በጨዋታ ዕለት ስብስቡ ላይ ይካተታሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ውጭ የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

እስከ አሁን በሊጉ 6 ያህል ጊዜ የተገናኙት ቡድኖች በ6 ግንኙነታቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ 1 አሸንፏል ፤ አንድ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሀምራዊ ለባሾቹ 11 ግቦችን አፄዎቹ በአንፃሩ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።