ሪፖርት | ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል

በወራጅ ቀጠናው ላይ እየዳከሩ የሚገኙትን እና ከቀጠናው በአንድ ደረጃ ብቻ ርቀው የሚገኙትን ቡድኖች ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።


ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በ29ኛው ሳምንት እየመሩ ቆይተው በሀዲያ ሆሳዕና 3ለ2 ሽንፈት ካስተናገዱበት ቋሚ ስብስባቸው አራት ለውጦችን አድርገው ፤ ናሆም ኃይለማርያም፣ ሳሙኤል ዩሐንስ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ዳዋ ሆቴሳን አሳርፈው በምትካቸው ሰለሞን ገመቹ፣ ኪሩቤል ወንድሙ፣ ሱልጣን በርሄ እና ዳዊት ገብሩን ይዘው ሲገቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩላቸው ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና 2ለ1 ከተሸነፉበት የመጀመሪያ ቋሚያቸው የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ አድርገው ቢኒያም በቀለን በጌታሁን ባፋ ተክተው ገብተዋል።

ሁለት ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን እንዲሁም በወራጅ ቀጠናው ላይ ያለ እና አንድ ደረጃ ብቻ ከቀጠናው ርቆ ያለውን ቡድን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ በተለይም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለነበሩት ቢጫ ለባሾቹ ወሳኝ ጨዋታ ነበር፤ ሳይጠበቁ ወራጅ ቀጠናው አከባቢ እራሳቸውን ላገኙት ለኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ነጥቡ አስፈላጊ ከመሆኑ አንፃር ጨዋታው ተጠባቂ ነበር።

ጨዋታው እንደተጀመረ ቢጫ ለባሾቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ሲደርሱ የተመለከትንበትን የመጀመሪያዎቹን አምስት ደቂቃዎች አሳልፈዋል። ከዚህ በኋላም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ጨዋታ ተመልሰው በእርጋት ኳስ ይዘው በመግባት ጥሩ እንቅሰቃሴ ያደረጉበትን አጠቃላይ አስር ደቂቃዎች ለመመልከት ችለናል።

የግብ ሙከራ በማድረግ ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ በእራሱ ጥረት ሳጥን ውስጥ ኳስ ይዞ በመግባት ያደረገው ሙከራ ለትንሽ ከፍ ይበልበት እንጂ ለግብ ቀርቦ የነበረ የኢትዮ ኤሌትሪክ የመጀመሪያ ሙከራ እንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ ላይ አንዋር በድሩ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በአጋማሹ ተጠቃሽ ነበር። በሙከራ አንፃር ወልዋሎዎችም በበኩላቸው አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ሳይጠቀሙ ሲቀሩ አስተውለናል።

በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቀዳሚ የመሆን ፍላጎታቸው ቢያሳዩም መሪ ለመሆን የነበራቸው ጉጉት ወደ ግብነት ወይንም ጠንካራ ወደሚባል ሙከራ ሊቀየር ሳይችል ቀርቷል። ይሁን እንጂ ቡድኖቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ቡድናቸው ሜዳ ክፍል በመድረስ ረገድ ደካማ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አላደረጉም። ይልቁንስ ጨዋታው እምብዛም ከሙከራዎች መታጀብ ባይችልም ጥሩ የኳስ ፍሰት በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተደርጓል። አጋማሹም ግብ ሳያስመለክተን 0ለ0 ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ከእረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጠንከር ብለው ተመልሰው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል፤ ከእነዚህም መካከልም በ49ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሽመክት ጉግሳ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ አቤል ሀብታሙ ወደ ግብ መጥቶ የቢጫ ለባሾቹ ተከላካዮች እንዴትም ተረባርበው ያውጡበት እንዲሁም በ57ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ሀብታሙ አግኝተው ሁለቱ ብቻቸውን ሆኖ ከግቡ ዘብ በረከት አማረ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠው ያመከኑበት አጋጣሚ እጅጉን አስቆጪ ቅፅበት ነበር።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲም በበኩላቸው በአንድ ለአንድ ቅብብል አልፈው አልፈውም ከተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ብናስተውልም ኳሶችን በቀላሉ እየተቀሙ እና ያለቁ ኳሶችን በደካማ አጨራረስ እያመከኑ ሲቸገሩ ተመልክተናል።

ሁለቱ ቡድኖች በፈጣን ሽግግሮች ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው ጎል ለማስቆጠር ጥረት ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም ይዘው የሚገቡትን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀይር አጨራረስ ላይ እየተቸገሩ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አምርቷል። በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በቀሐጥር በርከት ብለው ከግማሽ ሜዳ አለፍ ብለው ጫና ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን ቢጣ ለባሾቹ በአንፃራዊነት ከሜዳቸው ወረድ ብለው የተጋጣሚያቸውን ጫና ለማቋቋም ወደ መከላከሉ ያደሉበትን ቀሪ ደቂቃዎች ሲያሳልፉ አስተውለናል።

ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጫናቸውን አተናክረው የተቃራኑ ቡድን ተከላካይ መስመር የፈተኑ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ከሽንፈት አንዷን ነጥብ ምርጫቸው ያደረጉ የሚመስሉት ቢጫ ለባሾቹ የሚቀመሱ አልሆኑላቸውም። መደበኛዌ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ የታየው ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው የገቡት ቢጫ ለባሾቹ በአንድ ለአንድ ቅብብል ገብተው ፉሀድ አዚዝ አደገኛ ሙከራ አድርጎ ኢድሪሱ አብዱላኢ እንዴትም ያገደበት ሙከራ ባለቀ ደቂቃ ለወልዋሎዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማስገኘት የቀረበ አደገኛ ሙከራ ነበር።  በዚህም ጨዋታው በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ የሚቆጠርበት ቢመስለም ያለ ግብ ለመጠናቀቀ ተገዷል።