ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ባህርዳር ከተማ ከ መቻል

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ባህርዳር ከተማ ከ መቻል

በስድስት ነጥቦች እና በአንድ ደረጃ የሚበላለጡት ባህርዳር ከተማ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር ነው።

በአርባ ሰባት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከመሪው ጋር ያላቸውን የአስራ ሦስት ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ጦሩ ይገጥማሉ

በሲዳማ ቡና ከገጠማቸው የአንድ ለባዶ ሽንፈት በማገገም ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ድል አድርገው በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ የተጋሩት የጣና ሞገዶቹ በቅርብ ሳምንታት በውድድር ዓመቱ የነበራቸውን የወጥነት ችግር ቀርፈዋል። በሊጉ እስከ 25ኛው ሳምንት ድረስ ተከታታይ ድሎች ሳያስመዘግብ ከቆየ በኋላ መቐለ 70 እንደርታ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መሪው መድንን ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከውጤቱም ባሻገር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ተሻሽሏል። የጣና ሞገዶቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ለሳምንታት የዘለቀው የማጥቃት ጥንካሬያቸው ማስቀጠል ባይችሉም ተከታታይ ድሎች ባስመዘጉባቸው ሳምንታት በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረውን የማጥቃት መስመራቸው ጉልህ መሻቻል አሳይቷል። ከዚህ ቀደም በመከላከሉ ረገድ ካላቸው ጥንካሬ በዘለለ ውጤታማና በወጥነት የዘለቀ የፊት መስመር ያልነበራቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በመጨረሻው ጨዋታ ውስን መቀዛቀዝ የገጠመውን የፊት መስመራቸን ወደ ቀድሞ ብቃቱ የመመለስ ስራ የሚጠብቃቸው ሲሆን ተጋጣሚያቸው ደግሞ ከባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ መረቡን አስከብሮ የወጣ እንደመሆኑ ከመሪው ጋር ያላቸውን ነጥብ ለማጥበብ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ደረጃ ማሳደግ ግድ ይላቸዋል።

በአርባ አንድ ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች አንድ ደረጃ አሻሽለው የሀዋሳ ከተማ ቆይታቸው ለማጠናቀቅ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል ማድረግ ይኖርባቸዋል

በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ መሪዎቹን የመጠጋት ዕድላቸውን ያባከኑት መቻሎች ከድል ጋር ከተራራቁ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የውድድር ዓመቱ ዋነኛ ድክመት ሆኖ የዘለቀው የአፈፃፀም ድክመቱ ሲሆን ቡድኑ እንደሚፈጥራቸው ዕድሎች በርከት ያሉ ግቦች ለማስቆጠር መቸገሩም በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ቡድን አሁንም በጨዋታዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እየያዘ መቀጠሉ እንዲሁም ወጥነት ቢጎድለውም ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከተጋጣሚዎቹ የተሻለ መንቀሳቀሱ እንደ ጠንካራ ጎን የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ግን በግብ ፊት ያለው ውስንነት  መቅረፍ ግድ ይለዋል።

ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ላይ  በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ድክመት የግብ ዕድሎችን ያባከነው መቻል በነገው ዕለት ጠንካራና በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ሦስት ክለቦች አንዱ የሆነውን ባህርዳር ከተማ በሚገጥምበት ጨዋታ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል፤ ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር በጨዋታው እንደ ወትሮ በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ላያገኝ የሚችልበት ዕድል ስለሚኖርም የሚገኙት ዕድሎች በመጠቀም የተዋጣለት ቀን ማሳለፍ ይኖርበታል።

በጣና ሞገዶቹ በኩል በንግድ ባንኩ ጨዋታ በአለርጂ ምክንያት ከጨዋታ ውጪ የነበረው መሳይ አገኘሁ እንዲሁም በድንገተኛ ሕመም በጨዋታው ላይ ያልነበረው ፍጹም ፍትሕአለው ለነገ ጨዋታ እንደሚደርሱ ሲረጋገጥ የተቀሩት የቡድን አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመቻል በኩል ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በጉዳት ምክንያት ያልነበሩት ምንይሉ ወንድሙ እና አማኑኤል ዮሐንስ ከጉዳታቸው ያገገሙ ሲሆን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ያለነበረው አብዱልከሪም ወርቁን ጨምሮ ሦስቱም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል። የቡድኑ ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ቢሆኑም ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ግን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ነገ እንደማይኖር ተጠቁሟል።

ሁለቱ ቡድኖች 9 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱ በእኩሌታ 3 ጨዋታዎች ስያሸንፉ 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ጦሩ 12፣ ሞገዱ 11 አስቆጥረዋል።