ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ስሑል ሽረ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ስሑል ሽረ

ሊጉ በደማቅ ድጋፍ የታጀበው የስምንት ሳምንታት የውቢቷ ሀዋሳ ቆይቷል ነገ ያጠናቅቃል፤ ሀድያ ሆሳዕና ደረጃውን ለማሻሻል ስሑል ሽረ ደሞ የመትረፍ ዕድሉን ለማለምለም የሚፋለሙበት ጨዋታም የመጨረሻ መርሐ-ግብር ነው።

በአርባ አንድ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ብያንስ የአንድ ደረጃ መሻሻል ልያስገኝላቸው የሚችል ድል ፍለጋ ስሑል ሽረን ይገጥማሉ።

በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ በተካሄደው የመጨረሻ መርሐ-ግብር ወልዋሎን በማሸነፍ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ነብሮቹ በጨዋታው ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስተው ያስመዘገቡትን ጣፋጭ ድል ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስቶ በአስራ አምስት ደቂቃዎች ውጤቱን ቀልብሶ ድል ማስመዝገቡ እንደ በጎ ጎን የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ግቦች ያስተናገደበት መንገድ ግን ጉልህ ድክመቶች የተስተዋሉበት ነበር። በርግጥ የመጀመርያው ግብ በፍፁም ቅጣት ምት የተቆጠረ ቢሆንም ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት ሂደት ግን የመከላከል እና የውሳኔ ድክመት የተስተዋለበት ነበር፤ ሁለተኛው ግብም በተመሳሳይ በግል የመከላከል ስህተት የተቆጠረ ነው። ይህንን ተከትሎ በነገው ዕለት በኋላ ክፍሉ የተስተዋሉ  ድክመቶች መቅረፍ የቡድኑ ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የተሳነውን የፊት መስመሩ ማስተካከል አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚጠብቃቸው ሌላው ስራ ሲሆን ተጋጣሚያቸው በቅርብ ሳምንታት ጥሩ የመከላከል ብቃት በማሳየት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑም ምናልባት ከባድ ፈተና ሊጠብቃቸው ይችላል።

በሀያ አንድ ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በ16ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው አዳማ ከተማ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

በሊጉ ለመትረፍ ከሚያስችለው የ14ኛ ደረጃነት በአስራ ሁለት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ከሌሎች ክለቦች አንፃር ሲታዩ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይበልጥ ለመውረድ አደጋ ተቃርበው ይታያሉ። ቡድኑ ሊጉ ሊጠናቀቅ የስድስት ሳምንታት ዕድሜ በቀረበት ጊዜ በ16ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው አዳማ ከተማ እንኳን በአራት ነጥቦች ለመራቅ ተገዷል። ይህንን ተከትሎ ወልዋሎን ተከትሎ ከሊጉ ላለመውረድ በነገው ዕለት ከተጋጣሚው በላይ ነጥቦቹ እጅግ የሚያስፈልጉት ጊዜ ላይ ይገኛል። በስሑል ሽረ በኩል ሊነሳ የሚችለው አወንታዊ ነጥብ ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች በማገገም ከሽንፈት መራቁ ቢሆንም አሁንም ከአቻ ውጤት በላይ ማስመዝገብ ባለመቻሉ ጉዞውን አክብዶታል። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ የተጋራው ስሑል ሽረ ድል ካደረገ አስር የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥራል። ቡድኑ አሁን ላለበት ደረጃ መነሻ የሆኑ በርከት ያሉ ድክመት መጥቀስ ይቻላል፤ ሆኖም በሊጉ ዝቅተኛውን የግብ መጠን ያስመዘገበ እንዲሁም በ1ኛው ሳምንት አዳማ ከተማ ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ላለፉት ሀያ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የማጥቃት ጥምረቱ የቡድኑ ቀንደኛ ድክመት ነው። የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ቡድን ባለፉት አምስት መርሐ-ግብሮች ከቀደመው ብቃቱ አንፃር ሲታይ መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱ ባይካድም በሚፈለገው መጠን የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም የተገኙት ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ጉልህ ክፍተት የሚታይበት የማጥቃት ጥምረቱ በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባቸው የቡድኑ ደካማ ጎኖች ናቸው።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሰመረ ሀፍታይ እና ከድር ኩሊባሊ ቀለል ወደ ያለ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በተጨማሪም ዳግም ኑጉሴ አሁንም ቅጣቱን ባለመጨረሱ ነገ የማይኖር ሲሆን የተቀረው የቡድኑ ስብስብ ግን ለመጨረሻው የሀዋሳ ጨዋታ ዝግጁ ነው። በስሑል ሽረ በኩል አምበሉ ነፃነት ገብረመድኅን ከቅጣት ተመልሷል፤ እንዲሁም ጉዳት ላይ የነበሩት ክብሮም ብርሀነ እና አላዛር ሽመልስ ከጉዳታቸው አገግመው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል። አቤል ብርሃነ ግን በጉዳት ምክንያት ከነገው ውጭ ሲሆን በመጨረሻው ልምምድ ብቻ የተሳተፈው ክፍሎም ገብረህይወትም የመሰለፉ ነገር አጣራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዘው እና ባዶ ለባዶ ከተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ውጭ ዘንድሮ ተገናኝተው ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።