ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ነብሮቹ ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ለማለት ኤሌክትሪኮች ደግሞ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ የሚፋለሙት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በአርባ ሁለት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከስሑል ሽረ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መልስ የሚያስመዘግቡት ውጤት  በቀጠናው ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር የደረጃ መሻሻል ወይም ማሽቆልቆል የሚያስከትል እንደመሆኑ በተጋጣሚያቸው ልክ ባይሆንም መርሐ-ግብሩ ወሳኝ ነው።

በሁለተኛው ዙር በውጣ ውረድ የተሞላ ወጥነት ያልነበረው ቆይታ የነበራቸው ነብሮቹ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በብዙ ረገድ ተቀዛቅዘዋል።
ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በተከናወኑ አስራ አንድ ጨዋታዎች ስድስት አቻ፣ ሦስት ሽንፈት እና ሁለት ድሎች ከማስመዝገቡ በተጨማሪ ከ12ኛ ሳምንት በኋላ በተከናወኑ መርሐ-ግብሮች ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ መቸገሩም ለወጥነት ችግሩ አንድ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ቡድኑ ከስሑል ሽረ ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት  ከሜዳ ውጭ ያሉ ጉዳዮች በቡድኑ ስነ-ልቦና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው በመግለፅ ችግሮቹ ከተፈቱ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘገቡ መግለፃቸው ይታወሳል። እንደ አሰልጣኝ ግርማ አስተያየት የቡድኑ መንፈስ በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንደ አንድ መነሻ መጥቀስ የሚቻል ሲሆን የማጥቃት ክፍል ውጤታማነት መቀነስም ሌላው ለወጥነት ችግሩ የሚጠቀሰው ምክንያት ነው።

የማጥቃት ጥምረቱ ሁለት ግቦች ብቻ ካስቆጠረባቸው የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ስድስት ጨዋታዎች በኃላ በተከናወኑ አምስት መርሐ-ግብሮች ስምንት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም አሁንም የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። ይህንን ተከትሎ በነገው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች የተጠቀሰውን ድክመት መቅረፍ ከነብሮቹ የሚጠበቅ ነው።

በሰላሣ ሦስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ነገ ላለመውረድ በሚደርገው ፍልሚያ ውስጥ ተስፋን የሚያልሙበት ጨዋታ ያደርጋሉ።

ድል ካደረጉ አራት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩና በሁለተኛው ዙር በተከናወኑ አስራ አንድ ጨዋታዎች
ሰባት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ኤሌክትሪኮች ካሉበት አጣብቂኝ ለመውጣት ወደ ድል መንገድ መመለስ ግድ ይላቸዋል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ ያሉባቸውን ድክመቶች መቅረፍ ይገባቸዋል፤ ቡድኑ በሀዋሳ ቆይታው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ መውጣቱ እንዲሁም በጨዋታዎቹ አስር ግቦች ማስተናገዱም የድክመቱ ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ በማጥቃት እና በመከላከሉ ረገድ የሚታይባቸውን ችግሮች መቅረፍ ከአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም የኋላ ክፍሉ  ከምንም በላይ አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሻ የቡድኑ ድክመት ነው። የነገው ተጋጣሚያቸው ምንም እንኳን የወጥነት ችግር ቢኖርበትም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረ እንደመሆኑም ከወትሮ በተሻለ የመከላከል ቁመና መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው ሰመረ ሀፍታይ  አገግሞ ለነገው ጨዋታ የሚደርስ ሲሆን ከድር ኩሊባሊ ግን በነገው ጨዋታ አይሳተፍም።ከዚህ በተጨማሪ ዳግም ንጉሴ ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን አስጨናቂ ፀጋዬ ግን በቅጣት ምክንያት ጨዋታው ያመልጠዋል። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በተቀሩት 3 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱም ቡድኖቹ እኩል አራት አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።