ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ድሬዳዋ ከተማን ከባህርዳር ከተማ ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ 2ለ1 በሆነ ውጤት ብርቱካናማዎቹን ተከታታይ ድል በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።


ድሬዳዋ ከተማ በሀዋሳ ቆይታ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ግብ ጠባቂውን አላዛር ማረነን በአብዩ ከሣዬ ተክተው ሲቀርቡ ባህርዳር ከተማ በበኩላቸው በ30ኛው ጨዋታ ሳምንት ከመቻል ጋር 0ለ0 ከተለያዩበት መጀመሪያ ቋሚያቸው አንድ ለውጥ አድርገው ፍፁም ዓለሙን በፍሬው ሰለሞን ተክተው ገብተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ ጅማሮውን ያደረገው የእለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በሊጉ ብርቱ ፉክክር እያደረገ የሚገኘውን ባህርዳር ከተማን በተቃራኒው በደረጃ ሰንጠረዡ ከወራጅ ቀጠናው ለትንሽ ፈቀቅ ብለው ደረጃቸውን ለማሻሻል እየጣሩ የሚገኙትን ድሬዳዋ ከተማዎችን አገናኝቷል።

በተመጣጣኝ ጨዋታ እንቅስቃሴ እስከ አስረኛው ደቂቃ በዘለቀው በዚህ ጨዋታ ቡድኖቹ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ይዘት ያለውን አጨዋወት ለተመልካች ቢያስመለክቱም ባህርዳር ከተማዎች ወደፊት በመሄድ ረገድ እና የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻለ የተንቀሳቀሰ ቡድን ነበር። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃራዊነት ኳስ ተቆጣጥረው ከራሳቸው ሜዳ መነሻ በሆኑ ኳሶች ብልጫ ለመውሰድ ይጣሩ እንጂ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው ጫና ለማሳደር ያልቻሉበትን የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች አሳልፈዋል።

የጣና ሞገዶቸ ካደርጓቸው ሙከራዎች መካከል፤ 4ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ወንደሰን በለጠ እግር ስር ደርሶ ሳጥን ውስጥ ሆኖ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ከግቡ ቋሚ ብረት ለትንሽ ርቆ ያለፈበት እና በ13ኛው ደቂቃ ላይ እራሱ ወንደሰን በለጠ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ አደገኛ የሚባል ሌላኛው  ሙከራ ይጠቀሳል።

ኳስ ተቆጣጥረው በፈጣን ሽግግር ወደፊት ይሄዱ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ 20ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል፤ መሃል ሜዳ አከባቢ ከፍሬው ሰለሞን ኳስ ቀምቶ ያገኘው አቡበከር ሻሚል በተከላካዮች መሃል የሰነጠቀለት ኳስ አቤል አሰበ ጉልበቱን እና ፍጥነቱን ተጠቅሞ በመድረስ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ሳይጠበቅ ግብ ያስተናገዱት የጣናው ሞገዶች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት በአጫጭር ኳስ ቅብብል በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል መድረሳቸውን አጠናክረው ቀጥለው የብርቱካናማዎቹን ተከላካይ መስመር የፈተኑ ኳሶችን ይዘው ሲገቡ አስተውለናል። በዚህም በተደጋጋሚ የተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል ደርሰዋል፤ ሆኖም ግን አስቆጪ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ብርቱካናማዎቹ መሪ በመሆናቸው የተነሳ የሚያገኙትን ኳስ ተረጋግተው ከሜዳቸው እያራቁ ተጋጣሚው ቡድን መረባቸውን እንዳይደፍር በጥሩ መከላከል እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አስመልክተውን አንደኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ 1ለ0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ብርቱካናማዎቹ ለተጨማሪ ግብ ወደ ሳጥን ገብተው በፍፁም ቅጣት ምት ግብ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል፤ 48ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብልል ኳስ ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት የባህርዳር ከተማ ተከላካዮች አቤል አሰበ ላይ በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቀጣት ምት ተሰጥቷተው አስራት ቱንጆ ወደግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

የግቦቹ መቆጠር እንቅስቃሴያቸውን ያልገታቸው ባህርዳር ከተማዎች በተስፋ ጠንካራ ሙከራዎችን አድርገዋል፤ 56ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ የቆመ ኳስ ወደ ግብ አሻምቶ ፍሬዘር ካሣ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ኳስ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት እራሱን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግሩም ሁኔታ በመቀስ ምት ድጋሚ ወደ ግብ መጥቶ ለሁለተኛ ጊዜ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ ምናልባትም የግብ ልዩነታቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ሊያደርጋቸው የቀረበ ሙከራ ነበር።

ምንም እንኳን በሁለት ግቦች ቢመሩም ወደ ጨዋታ ሊመልሳቸው የሚችል አንድ ግብ ፍለጋ ያለመታከት በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጉ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች በ70 ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ግብ አግኝተዋል፤ በረጁም የተጣለ ኳስ ቸርነት ጉግሳ ጋር ደርሶ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ሙጂብ ቃሲም አሻግሮለት ተረጋግተው በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነታቸውን ወደ አንድ ዝቅ እንዲል አደርጓል።

2ለ1 በሆነ ውጤት የግብ ልዩነት ከጠበበ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግር ጨዋታው ግለቱን ጨምሮ ሲቀጥል ብርቱካናማዎቹ ነጥቡን አስጠብቀው ለመውጣት ከሚያደርጉት መከላከል ጋር አልፈው አልፈው ልዩነቱ አንድ ብቻ መሆኑ አስተማማኝ ስላልሆነ ልዩነት ለማስፋት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ አስተውለናል። የጣናው ሞገዶች በበኩላቸው ጫን ብለው የአቻነት ግባቸውን ለማግኘት ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን እየደረሱ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ እንዳያፈራ እጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ  ለማስጠበቅ ጠንከር ያለ መከላከል ላይ ያተኮሩት የብርቱካናማዎቹ ተጫዋቾች ሙከራቸውን ሲያግዱባቸው አስተውለናል።

ጨዋታው የእለቱ ዋና ዳኛ የመጨረሻ ፊሽካቸውን እስኪያሰሙ ድረስ ግብ የሚቆጠርበት እየመሰለ ቢቀጥልም ብርቱካናማዎቹ በሁለቱም አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2ለ1 በሆነ ውጤት የጣናውን ሞገድ በማሸነፍ ተጨማሪ ሶስት ነጥብ ወደ ካዝናቸው አስገብተው ጨዋታው ተቋጭቷል።