አሠልጣኝ ፍሬው በዩጋንዳ የሊግ ዋንጫ ባለቤት ሆነዋል

አሠልጣኝ ፍሬው በዩጋንዳ የሊግ ዋንጫ ባለቤት ሆነዋል

በዩጋንዳ የሴቶች ከፍተኛው የሊግ እርከን ተሳታፊ የሆነውን ካምፓላ ኩዊንስ ቡድን እያሰለጠኑ የሚገኙት አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከቡድናቸው ጋር ሻምፒዮን ሆነዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት እና ዋናው ቡድን አሠልጣኝ የነበሩት ፍሬው ኃይለገብርኤል በ2016 አጋማሽ ላይ ለአራት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጡበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተነሱ በኋላ ወደ ዩጋንዳ ሊግ በማምራት ከስድስት ወራት በፊት የካምፓላ ኩዊንስ የሴቶች ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። በፉፋ የሴቶች ሱፐር ሊግ የሚሳተፈውን ቡድን ከተረከቡ በኋላ በመልካም የውጤት መንገድ ቡድኑን ሲመሩ የነበሩት አሠልጣኙ ዛሬ ከሜዳቸው ውጪ ቶሮ ኩዊንስን ገጥመው አንድ አቻ ከተለያዩ በኋላ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸውን አረጋግጠዋል።

ከዚህ የውድድር ዓመት በፊት አንድ ጊዜ የፉፋን ሱፐር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ካምፓላ ኩዊንስ የዘንድሮውን የውድድር ዓመትን በአሠልጣኝ ቻርለስ አይኮህ እየተመራ ቢጀምርም ከ5 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚጠበቅበት 15 ነጥቦች ዘጠኙን ብቻ በማሳካቱ ከክለቡ ከተነሳ በኋላ አሠልጣኝ ፍሬው መንበሩን ተረክበው ቡድኑን የሊጉ መሪ በማድረግ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ከኩዋምፔ ሙስሊም ሌዲስ ክለብ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት 4 አድርሶ አንድ ጨዋታ እየቀረው የዋንጫው ባለቤት መሆኑ ተረጋግጧል።

ከቀናት በፊት ይፋ የሆነው አዲሱን የፉፋ ሴቶች ሱፐር ሊግ ዋንጫ የዛሬ ሳምንት ካምፓላ ኩዊንስ ከሺ ማሩንስ ጋር በሚደረገው የመጨረሻ ጨዋታ በይፋ የሚረከብ ይሆናል።