ከወራቶች በፊት ለግብጹ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ፊርማውን አኑሮ ውሉ ሳይጠናቀቅ ክለቡ ማሰናበቱን ተከትሎ ወደ ፊፋ ያመራው አቤቱታ ውሳኔ አግኝቷል።
በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ ለሁለት ዓመታት ቆይታን ለማድረግ ወደ ግብጹ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ያቀናው የመስመር ተከላካዮ ሄኖክ አዱኛ ያለ ተጫዋቹ ፍቃድ የውል ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ክለቡ ውሉን መቅደዱ እና ሄኖክም ወደ ሀገርቤት መመለሱ ፤ ጉዳዮንም ወደ ፊፋ ይዘውት እንደሚሄዱ ወኪሉ አዛርያስ ተስፋጽዮን ገለጻልን እንደነበረ ከዚህ ቀደም መረጃውን አድርሰናቹሁ ነበር።
አሁን እንደደረሰን መረጃ ከሆነ ጉዳዮን ሲመለከት የነበረው የፊፋ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የውል ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ክለቡ ውሉን ያለ ተጫዋቹ ፍቃድ ማቋረጡን ተከትሎ ሃራስ ኤል ሁዶድ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን ይህን ክፍያ ክለቡ በአርባ አምስት ቀናት ውስጥ ተፈፃሚ የማያደርግ ከሆነ የተጫዋቾች ዝውውርን ማድረግ እንዳይችል እንደሚታገድ ፊፋ አሳውቋል።
በአሁን ሰዓት ሄኖክ አንዱኛ ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም ከወኪሉ ጋር በካይሮ የሚገኝ ሲሆን ከሰሞኑ ወደ ሀገር ቤት የሚመለስ ይሆናል።