ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የዓመቱን አስራ ሁለተኛ ድል አሳክቷል

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የዓመቱን አስራ ሁለተኛ ድል አሳክቷል

ሲዳማ ቡና በብርሀኑ በቀለ ብቸኛ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 በሆነ ውጤት በመርታት ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ ፈረሰኞቹ በአንፃሩ አስራ አንደኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።


በሀዋሳ የመጨረሻ ጨዋታቸው ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀዋሳ ከተረታው ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን ከረታው ስብስባቸው በተመሳሳይ የሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ፈረሰኞቹ ተመስገን ዮሐንስን በባህሩ ነጋሽ ፣ ሀብታሙ ጉልላትን በሔኖክ ዮሐንስ ቡናማዎቹ ሬድዋን ናስርን በአስቻለው ሙሴ ደስታ ደሙን በጊት ጋትኩት ተክተው ቀርበዋል።

የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ የሆነው ጨዋታ ዘጠኝ ሰዓት ሲል ተጀምሯል። የጨዋታውን አስር ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚመስልን እንቅስቃሴን ለማስመልከት ቡድኖች ጥረት ያደረጉ ቢመስልም በተጠቀሰው ደቂቃ ሜዳ ላይ በሚንፀባረቀው መጠነኛ የሐይል አጨዋወት በስተቀር እምብዛም የተሳኩ ጥረቶችን አላስተዋልንበትም ይልቁንም ሰባተኛ ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አጥቂ ማይክል ኪሩፕሮፕ በጉዳት በይገዙ ቦጋለ የተተካበት ሁነት በልዩነት ልትጠቀስ የምችለዋ አጋጣሚ ሆናለች። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ኳስን ለመቆጣጠር ፈረሰኞቹ ውስን ትጋት ቢያሳዩም ወደ ግራ በይበልጥ በመሳብ ሲጫወቱ የታዩት ሲዳማ ቡናዎች የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል እንደ ልብ መጎብኘት ጀምረዋል።

13ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ አብረሀም ጌታቸው ለማቀበል ሲል ለይገዙ የሰጠውን ኳስ ተጫዋቹ ወደ ግብ ሳጥን ጠርዝ ሆኖ የመታውን ኳስ ባህሩ ነጋሽ የያዘበት እና ከደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ በተፈጠረ የቅብብል ስህተት ሀብታሙ ታደሠ ያገኘውን ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን የደረሰውን ኳስ ወደ ውስጥ ጠልቆ ገብቶ መሬት ለመሬት ሲመታው  የግብ ዘቡ ባህሩ ነጋሽ ተቆጣጥሮበታል። ከራሳቸው ሜዳ በቅብብል ወደ ተቃራኒው የሜዳ ክፍል ሲገቡ ድክመቶችን ጎልቶ የታየባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች መስፍን ታፈሠ ካደረጋት ሙከራ እና ባህሩ ካወጣት ክስተት መልስ ጎል አስተናግደዋል።

37ኛው ደቂቃ ጊት ጋትኩት ከራሱ ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባህሩ እና የመሐል ተከላካየች የውሳኔ ደካማነት ታክሎበት ብርሀኑ በቀለ በግንባር ገጭቶ ከመረብ አዋህዶ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል። በጭማሪው የመገባደጃ ደቂቃዎች ውስጥ ሀብታሙ ታደሠ ከቀኝ በኩል ከይገዙ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀምበት ከቀረ በኋላ አጋማሹ ተገባዷል።

ከመጀመሪያው ከፍ ብሎ የተመለሰው ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ጎል የደረሰቡት ቢመስልም በሂደት ኳሱን ወደ ራሳቸው በማድረግ መንቀሳቀስን የመረጡት ፈረሰኞቹን መጠነኛ የበላይነትን ቢይዙም ለኋላ ክፍላቸውን ኮስታራነትን ጨምረው የታዩት ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት በተቃራኒው ዕድሎችን የፈጠሩበትም ነበር። የጨዋታውን አካፋይ ደቂቃዎች ወደ ሳጥን ቶሎ ቶሎ መጠጋትን መርጠው የታዩት ፈረሰኞቹ በሁለቱም አማኑኤሎች በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ካለ መረጋጋት በተነሳ ሳይጠቀሟቸው ቀርተዋል።

ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ደጋግመው እንደመድረሳቸው ጥራት ያላቸውን ዕድሎች ፈጥረው የጎሉን መረብ ማግኘቱ የከበዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካያቸው አሸናፊ ጌታቸው የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ሀብታሙ ታደሠ ካልተጠቀማት አጋጣሚ በኋላ 80ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበውም ነበር። በጥሩ ቅብብል ሳጥን ጠርዝ የተገኙት ሲዳማዎች በዛብህ መለዮ ከሀብታሙ የደረሰውን ወደ ግብ አክርሮ መቶ የባህሩ ቅልጥፍና ታክሎበት ኳሷን ከግብነት መክናለች።


ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ አቤኔዘር አስፋው የሲዳማን የግብ መጠን ከፍ የምታደርግ አማኑኤል ኤርቦ ፈረሰኞቹን አቻ የምታደርግ ጎልን ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በመባላቸው ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1ለ0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።