የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰንጠረዡ አካፋይ ለመሻገር አዳማ ከተማ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው የሚወጣበትን ዕድል ለማለምለም የሚያደርጉት ፍልምያ ተጠባቂ ነው።
በሰላሣ ዘጠኝ ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከአምስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል ለማድረግ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል ተብሎ ከሚጠበቀው አዳማ ከተማ ጋር ይፋለማሉ።
በ25ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፉ በኋላ በተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ድል ያልቀናቸው ሀምራዊ ለባሾቹ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ላይ በመደዳ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።
በቅርብ ሳምንታት ተከታታይ የአቻ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ ደረጃውን የማሻሻል ዕድሉ ያባከነው ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ጉዞው በአቻ ውጤቶች የተቆራኘ ነው፤ በሊጉ በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ቀዳሚ ከሆነው ስሑል ሽረ በመቀጠል በርከት ባሉ ጨዋታዎች ነጥብ የተጋራ መሆኑም የዚህ ማሳያ ነው። ሀምራዊ ለባሾቹ ከመሪው መድን እና መቻል በመቀጠል ከሌሎች ክለቦች ጋር በጣምራ ጥቂት ሽንፈቶች በማስተናገድ በ3ኛ ደረጃ መቀመጥ ችለዋል።
ሆኖም ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ጥቂት ሽንፈት ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ የሚመደብ ቢሆንም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ከማጠናቀቅ አባዜው መላቀቅ ባለ መቻሉ ደረጃው አሽቆልቁሎታል።
ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ ቡድኑ ከጨዋታ ብልጫ በዘለለ ውጤታማ የማጥቃት ክፍል መገንባት አለመቻሉ ሲሆን በቀጣይ መርሐ-ግብሮችም የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ የማድረግ ስራ ይጠብቀዋል።
በሀያ ስድስት ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በመቀመጫ ከተማቸው እና በደጋፊያቸው ፊት የተሻለ ውጤት አስመዝግበው በሊጉ የሚያቆያቸውን ነጥብ ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጉዞ ነገ ይጀምራሉ።
ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ተስፋቸው ያለመለሙት አዳማ ከተማዎች በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በ15ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ያላቸውን የአራት ነጥቦች ልዩነት ማጥበብ አልቻሉም።
አዳማ ከተማዎች በውጣ ውረዶች፣ በተከታታይ ሽንፈቶች የተሞላ ደካማ የውድድር ዓመት አሳልፈዋል። ካስመዘገቡት ነጥብ ባሻገር በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ከወልዋሎ ጋር በጣምራ ቀዳሚ መሆናቸው፤ በርከት ያሉ ሽንፈቶች በመቅመስ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው እንዲሁም ጥቂት ድሎች ካስመዘገቡ ሦስት ክለቦች ተርታ መመደባቸውን የደካማ ውድድር ዓመቱ ማሳያ ነው።
ሆኖም ከዚ ሁሉ የዝቅታ ጉዞ በኋላ በደጋፊያቸው ፊት በሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካስመዘገቡ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር የሚያስጠጋቸው ዕድል ስለሚሰጣቸው መርሐ-ግብሩ እጅግ ወሳኝ ነው።
ከዚህ ቀደም ውድድሩ ከ12ኛው እስከ 22ኛው ሳምንት ድረስ በመቀመጫ ከተማቸው በተካሄደበት ወቅት በአስር የጨዋታ ሳምንታት ቆይታ ስድስት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በደጋፊያቸው ፊት ደካማ ውጤት ያገኙት አዳማ ከተማዎች በቀሩት የቡድኑ የፕሪምየር ሊጉ ቆይታ የሚወስኑ ስድስት ወሳኝ መርሐ-ግብሮች ደካማው የሜዳቸውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በሦስት መርሐ-ግብሮች ላይ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ውስን መሻሻል ካሳየ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ድክመት ማረም እንዲሁም በተለይም በቅርብ ሳምንታት ጥሩ መሻሻል ብያሳይም ጉልህ የአፈፃፀም ችግር የተስተዋለበትን የፊት መስመራቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ባሲሩ ኡማር በጉዳት ብሩክ እንዳለ ደግሞ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በአዳማ ከተማ በኩል በቅርቡ ከባድ ጉዳት ያስተናገደው አሜ መሐመድ ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው፤ እንዲሁም ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ለጨዋታው የመድረሱ ጉዳይ ነገ የሚረጋገጥ ሲሆን ከጨዋታው ውጪ የመሆን ዕድሉ የሰፋ መሆኑም ታውቋል፤ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን በሙሉ ጤንነት ይገኛሉ።
ቡድኖቹ በሊጉ 34 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 18 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። አዳማ ከተማ 4 ጨዋታ ሲያሸንፍ በ12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ባንክ 58 ጎሎች ሲያስቆጥር አዳማ 29 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።