በአንድ ነጥብ ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡትን ክለቦች ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በአርባ አንድ ነጥብ 7 ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል በአንድ ነጥብ ልቆ 6ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቻል ይፋለማሉ።
በአዳማ ከተማ በተከናወኑ የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ አራት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ውጤታማ ጊዜ ያሳለፉት የጦና ንቦቹ ወደ ሀዋሳ ካቀኑ በኋላ የቀደመው ውጤታማነታቸውን ማስቀጠል አልቻሉም። ቡድኑ በሀዋሳ ቆይታው ሸገር ከተማን አሸንፎ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑ ብያረጋግጥም በሊጉ ግን ደካማ ውጤት አስመዝግቧል። በሀዋሳ የስምንት ሳምንታት ቆይታ ውስጥ አራት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገቡ እንዲሁም በአጠቃላይ በሊጉ ከገጠሙት ስምንት ሽንፈቶች ውስጥ አራቱ በሀዋሳ ከተማ የተመዘገቡ መሆናቸውም የዚህ ማሳያ ነው።
ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ላስመዘገባቸው ደካማ ውጤቶች በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም በመከላከሉ እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ውጤታማነት መቀነሱ ግን ዋነኞቹ ናቸው። የተከላካይ ክፍሉ ከ18ኛው እስከ 24ኛው ሳምንት በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ በስድስቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ካስተናገደ በኋላ በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስተናገዱ የማጥቃት ጥምረቱ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ በተካሄዱ ስምንት መርሐ-ግብሮች ውስጥ በአራቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ መውጣቱም ቡድኑ በፊት እና ኋላ ክፍሎቹ ያሉበትን ድክመቶች ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ የተጠቀሱትን ድክመቶች ማረም ከአሰልጣኙ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።
አርባ ሁለት ነጥብ በማስመዝገብ ከነገው ተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ ልቀው 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ከሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
መቻል በሀዋሳ የስምንት ሳምንታት ቆይታው አንድ ሽንፈት ብቻ የቀመሰ ቢሆንም ከተመዘገቡት ውጤቶቹ ግማሾቹ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ መሆናቸው ደረጃው እንዳያሻሽል እክል ሆኖታል። ቡድኑ ባለፉት ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ከሽንፈት መራቁ እንዲሁም ከመጨረሻዎቹ ስምንት መርሐ-ግብሮች ውስጥ በአምስቱ መረቡን አስከብሮ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም የመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ መጋራቱ እና ከድል ጋር መራራቁ ግን ወደ ሰንጠረዡ አናት ከፍ እንዳይል አድርጎታል። መቻሎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ በላይ መሻሻል የሚሰጣቸው ባይሆንም ወገብ ላይ ለመደላደል ግን ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው የመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም ወጥነት የሚጎድለውን የግብ ማስቆጠር ብቃታቸውን ማስተካከል ደግሞ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን የሚጠበቅ ነው።
ወላይታ ዲቻዎች በቅጣትም ሆን በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። መቻል በነገው ጨዋታ አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁን በጉዳት ምክንያት የሚያጣ ይሆናል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 19 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 8 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻሎች ደግሞ 6 ጊዜ አሸንፈው ቀሪዎቹ 5 ግንኙነቶች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። የጦና ንቦቹ 18 እንዲሁም ጦሩ ደግሞ 17 ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።