ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል

ሀዲያ ሆሳዕናን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ሦስተኛው መርሐግብር 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።


ገና ጨዋታው እንደጀመረ በማለዳው ወደ ተጋጣሚያቸው ቡድን ግብ ክልል መድረስን ምርጫቸው ያደረጉት ከቤራዎች ጥረታተው ተሳክቶ በሦስተኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ በየነ ባንጃ ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ፀጋአብ ግዛው ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ አድርጓቸዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላም ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ተቆጣጥረው ይጫወቱ እንጂ መረጋጋት ተስኗቸው ኳሶች እተቆራረጡባቸው ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ለመድረስ ሲቸገሩ አስተውለናል። በዚህም ጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አካፋይ እስኪደርስ ድረስ ሁኔኛ ግልፅ የሆነ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። በ22ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ ከሳጥን ውጪ ሆኖ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ጠንክር ያለ የኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሙከራ ነበር።

ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአቻነት ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ገብረህይወት ከእራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ከተካላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ አቤል ሀብታሙ በፍጥነት ደርሶ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ጋር አገናኝቶ አቻ አድርጓቸዋል።

አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ጨዋታ እንቅስቃሴ ወደፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም በጥንቃቄ በመጨዋታቸው የተነሳ ጠንከር ያለ ሙከራ ሲያደርጉ ሳናስተውል አጋማሹ ወደመገባደጃው ተቀርቧል። እንዲሁም ሀይል የተቀላቀለ አጨዋወት በመከተላቸው በተደጋጋሚ በቆሙ ኳሶች ጨዋታው እየተቋረጠ ሲቀጥል ተመልክተናል። በ38ኛው ደቂቃ ላይ ጌታሁን ባፋ ኢዮብ አለማየሁ ላይ በሰራው ጥፋት አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት ምት አግኝተው በብሩክ ማርቆስ አማካኝነት ወደ ግብ መጥተው ኢድሪሱ አብዱላሂ እንዴትም ያገደበት የሀዲያ ሆሳዕናዎቹ አደገኛ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። አጋማሹም በአቻ ውጤት ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል በዚህም ኢዮብ ገብረማርያም በአሸናፊ ጥሩነህ ተቀይሮ ወጥቷል። ሀዲያ ሆሳዕና በበኩላተቸው የተጫዋች ቅያሪ ሳያደርጉ ተመልሰዋል። አጋማሹ እንደተመለሰ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዋሚሾ በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ያሻገረውን ኳስ ኢዮብ አለማየሁ ወደ ግብ መጥቶ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው ያወጡባቸው ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ይታወሳል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የጨዋታ አቀራረባቸውን ቀይሮ የገቡ ሲሆን በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ለመሄድ ጭረት እያደረጉ ነገር ግን ግልፅ በሆኑ ሙከራዎች ሳይታጀብ ጨዋታው ወደ ስልሳዎቹ ዘልቋል። በተጨማሪም ቡድኖቹ መረጋጋት ተስኗቸው የተሳካ የኳስ ቅብብል ለማድረግ እንኳን ሲቸገሩ አስተውለናል። 61ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ አቤል ሀብታሙ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ስንታየሁ ታምራት በቀላሉ የተቆጣጠረበት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሙከራ ይጠቀሳል።

ጥሩ የማሸነፍ ተነሳሽነት በታየው በዚህ ጨዋታ ቡድኖቹ የጨዋታውን ሂደት የቀየረች ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ቶሎ ቶሎ መሮጣቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉም በተቃራኒ ቡድናቸው ላይ የነበረው የጥንቃቄ አጨዋወት የግብ እድል ለመፍጠር አመቺ ሊሆንላቸው ሳይችል ቀርቶ ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች አምርቷል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በመልሶ ማጥቃት በረጃጅም ኳሶች በተመጣጣኝ ጨዋታ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድች ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በሙሉ ሀይላቸው በቁጥር በርከት ብለው እያጠቁ እንዲሁም በአንድነት መከላከሉ ላይም እየተሳተፉ ጥሩ የጨዋቴ እንቅስቃሴ ቢያስመለከቱንም ወደ ግብ ደርሰው የሚያደርጉት ሙከራ ተጋጣሚ ቡድናቸውን ከመፈተን የዘለለ ኢላማውን የጠበቀ አደገኛ ሙከራ ሳይሆይ ቀርቶ ጨዋታው በመጀመሪቻ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።