አዳማ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ባደረጉት ቅያሪዎች ታግዞ በነቢል ኑሪ ሁለት ጎሎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ0 በመርታት የዓመቱን ሰባተኛ ድል ሲያሳካ ሀምራዊ ለባሾቹ በበኩላቸው ስምንተኛውን ሽንፈት አስተናግደዋል።
በሀዋሳ የመጨረሻ ጨዋታቸው ከፋሲል ጋር 1ለ1 የተለያዩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ተስፋዬ ታምራትን በኤፍሬም ታምራት ፣ በዛብህ ካቲሶን በናትናኤል ዳንኤል ሲተኩ በኢትዮጵያ ቡና 2ለ0 በተረቱት አዳማዎች በኩል ደግሞ በተደረገ የአምስት ተጫዋቾች ቅያሪ ዳግም ተፈራ ፣ መላኩ ኤልያስ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ ነቢል ኑሪ እና ቢኒያም ዐይተን ወጥተው ናትናኤል ተፈራ ፣ ሬድዋን ሸረፋ ፣ አቤኔዘር ሲሳይ ፣ ሱራፌል ዐወል እና አብዱልፈታህ ሰፋ ተክተዋቸው ገብተዋል።
የሳምንቱ የሦስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በፌዴራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ እየተመራ ጀምሯል። ንግድ ባንክ በተከታታይ እያጣ የመጣውን የአሸናፊነት መንፈስ ለመመለስ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ከወራጅ ስጋት ውስጥ ሊወጡ የሚችሉበትን ውጤት ለመያዝ ወሳኝነቱ ከፍ ባለው የቡድኖቹ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ከተጠበቀው በታች ደከም ያለ ፉክክርን አስመልክቶናል። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች መጠነኛ የኃይል አጨዋወትን የተመለከትን ሲሆን አዳማ ከተማዎች በአብዱልፈታህ ሰፋ በጨዋታ ው ጅማሪ ላይ ደካማ የቅጣት ምት ሙከራን ከመመልከታችን በቀር ጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር።
ንግድ ባንኮች በፈጣን ሽግግር ከመስመር የማጥቂያ መነሻቸውን በማድረግ አዳማ ከተማዎች በአንፃሩ ከኋላ ክፍላቸው መስርተው ከሚያደርጉት ንክኪዎች ከኋላ ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች መጫወት መርጠው ቢታዩም ጨዋታው ግን ከእንቅስቃሴ የዘለለ ፉክክር አልታየበትም ይልቁንም 28ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ አጥቂ ናትናኤል ዳንኤል ባስተናገደው ጉዳት በበዛብህ ካቲሶ ተቀይሮ የወጣበት ምንአልባትም በልዩነት በጨዋታው ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ነው።
33ኛው ደቂቃ መነሻዋን ከሳይመን ፒተር አድርጋ በዛብህ አመቻችቶ ከሳጥኑ የቀኝ ቦታ ላይ ለተገኘው ኪቲካ ጀማ ሰጥቶት ቢመታውም የውጪውን መረብ ኳሷ ነክታ መውጣት ከቻለችበት ሙከራ ውጪ በብዙ መመዘኛ ደካማ የነበረው አጋማሽ ያለ ጎል ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ አዳማዎች አብዱልፈታህ ሰፋ እና ሱራፌል ዐወልን በነቢል ኑሪ እና ሙሴ ኪሮስ ከለወጡ በኋላ ጨዋታው ቀጥሏል። ተመጣጣኝ የሚመስልን ነገር ግን በንፅፅር አዳማ ከተማዎች በፍላጎት ከፍ ያለውን እንቅስቃሴ እያደረጉበት የቀጠለው አጋማሹ ቡድኖቹ በተመሳሳይ መልኩ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ ደርሰው ይስተዋል እንጂ የነበራቸው ጥድፊ እና መቻኮሎች በአጋማሹ ጥራት የታከለባቸውን አጋጣሚዎችን እስከተወሰኑ ደቂቃዎች ድረስ እንዳንመለከት ዳርጎናል። ከሰባኛው ደቂቃ በኋላ አሸናፊ ኤልያስ እና ቢኒያም ዐይተንን ወደ ሜዳ ቀይረው ካስገቡ በኋላ ማጥቃታቸው ላይ ጉልበትን የጨመሩት አዳማዎች 74ኛው ደቂቃ በአጋማሹ በቀየሯቸው ተጫዋቾች ከተደረጉ ንክኪዎች በኋላ ጎልን አግኝተዋል።
ነቢል ኑሪ ራሱ ከግራ መስመር ያስጀመረውን ኳስ ቢኒያም ደርሶት ወደ ጎል መቶ በተከላካይ ተደርባ ወደ ቀኝ የሄደችን ኳስ አሸናፊ ወደ ጎል ሞክሮ በግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን ስትመለስ ኳሷን ያገኘው ነቢል ኑሪ መረቡ ላይ ደባልቋት አዳማን መሪ አድርጓል። ጎልን ካስቆጠሩ በኋላ ፍፁም ብልጫውን በተጋጣሚያቸው ላይ ያሳደሩት የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ተጫዋቾች 81ኛው ደቂቃ ላይም ሁለተኛ ጎላቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል።
ሌላኛው ተቀይሮ የገባው ሙሴ ኪሮስ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ነቢል ኑሪ በግንባር ገጭቶ የፍሬውን እጆች ኳሷ ከነካካች በኋላ ወደ ጎልነት ስትቀየር ተጫዋቹም በጨዋታው ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎሉን አክሏል። ንግድ ባንኮች 88ኛው ደቂቃ ላይ በአዲስ ግደይ አደገኛ የቅጣት ምት ሙከራን ከሰነዘሩ በኋላ ጨዋታው በመጨረሻም በአዳማ ከተማ የ2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም አዳማ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው እንዲወጣ የሚረዳው የዓመቱ ሰባተኛ ድሉ ሆኖ ሲመዘገብ ንግድ ባንኮች በአንፃሩ ስምንተኛውን ሽንፈት አስተናግደዋል።