መቻሎች በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ከጦና ንቦች ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ መጋራት ችለዋል።
31ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ የዕለቱ መርሐግብር ሁለተኛ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከ መቻል ጋር አገናኝቷል። ድቻዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ቡና ከተሸነፉበት የጨዋታ አሰላለፍ 6 ተጫዋቾችን ሲቀይሩ ግብጠባቂውን ቢንያም ገነቱ፣ መልካሙ ቦጋለ፣ ፍፁም ግርማ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ መሳይ ሰለሞን እና ፀጋዬ ብርሃኑ አስወጥተው በምትካቸው አብነት ይስሃቅ፣ አዛሪያስ አቤል፣ ዮናታን ኤልያስ፣ ናትናኤል ናሴሮ፣ መሳይ ኒኮል፣ ያሬድ ዳርዛን ሲያስገቡ መቻሎች በበኩላቸው ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ ግሩም ሀጎስ፣ ዮሐንስ መንግሥቱ እና በኃይሉ ግርማን በማሳረፍ በእነርሱ ምትክ ፍሪምፖንግ ሜንሱ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ፊሊሞን ገብረጻዲቅን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ምሽት 12:00 ሰዓት ሲል የተጀመረው ጨዋታ በጨዋታው ጅማሮ ላይ በነበሩ 15 ያክል ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተቀራራቢ የሚባል ብልጫ ሲኖራቸው የተቀሩትን ደቂቃዎች ግን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ መቻሎች ብልጫ ነበራቸው። በኳስ ቁጥጥሩ መቻሎች ብልጫ መውሰድ ቢችሉሞ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ደርሰው የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ደካማ ነበሩ። ወላይታ ድቻዎችም በመልሶ ማጥቃት አጥቂያቸውን ካርሎስ ዳምጠው ዒላማ ያደረገ በረጅሙ የሚጣል ኳስ ላይ ትኩረት ቢያደርጉም እነሱም የግብ ሙከራን ለማድረግ ተቸግረው ነበር።
በፊሊሞን ገብረጻዲቅ አማካኝነት ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ የሞከረው እና በግቡ አግዳሚ አናት ላይ ከወጣው ቀለል ያለ ሙከራ በስተቀር ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለሙከራ የቆየው አጋማሹ 39ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከድቻ ተከላካይ ኳስ በመንጠቅ በግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የመታው ኳስ ጎል ነው ተብሎ የመቻል ተጫዋቾች ደስታቸውን ለመግለጽ በተዘጋጁበት ሰዓት ውብሸት ክፍሌ በፍጥነት ጎሉ ላይ በመድረስ ኳሷን የግቡ መስመር ላይ በመመለስ ክለቡን መታደግ ችሏል። ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከፍተኛ በሆነ መነቃቃት ወደ ሜዳ የገቡት ወላይታ ድቻዎች ወዲያው መሪ መሆን የቻለበትን ግብ አስቆጥረዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ እና አብነት ደምሴ ጥሩ በሆነ አንድ ሁለት ቅብብል ይዘው በመግባት ያሬድ ዳርዛ በሳጥኑ የግራ ክፍል ሁኖ ያቀበለውን ኳስ ዮናታን ኤልያስ ወደ ግብነት ቀይሮ ሜዳ ውስጥ የሚገኙ ደጋፊዎችን በደስታ ማስፈንጠዝ ችሏል።
መቻሎች ባላሰቡት ሰዓት እና አይነት ከተቆጠረባቸው ድንገተኛ ግብ በኋላ ወደ ጨዋታ በመመለስ የጨዋታውን ብልጫ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወስደው የአቻነት ግብ ለማግኘት በተደጋጋሚ በቁጥር በመብዛት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ጫናዎችን ፈጥረው መድረስ የቻሉ ሲሆን መቻሎች በኮሊን ኮፊ፣ ዳዊት ማሞ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግብ ለማስቆጠር ግን ተቸግረው ተስተውለዋል። ወላይታ ድቻዎች በቁጥር በዛ ብለው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በመጫወት የግባቸውን መረብ ላለማስደፈር እጅግ ሀይለኛ ትንቅንቅ ማድረግ ችለዋል።
መቻሎች የአቻነት ግብ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ የተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ተጠናቀው የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት የድቻዎችን ተስፋ ያጨለመ ግብ መቻሎች ማስቆጠር ችለዋል። 97ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ገፋ አድርጎ የሰጠውን ኳስ ኮሊን ኮፊ ከርቀት አክርሮ በመምታት ድንቅ የሆነ ግብ አስቆጥሮ ባለቀ ሰዓት ክለቡ ነጥብ እንዲጋራ አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ እስከመጨረሻው ደቂቃ ከባድ የሆነ ትንቅንቅን ያስመለከተን ጨዋታ መቻሎች ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሩት ግብ 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።