የጣና ሞገዶቹ ጨርሶ ያልጠፋው የዋንጫ ዕድላቸውን ለማለምለም አዞዎቹ ደግሞ ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በአርባ ስምንት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች መሪዎቹን የመጠጋት ዕድላቸውን ካባከኑበት የመጨረሻው ሽንፈት ለማገገም አዞዎቹን ይገጥማሉ።
የጣና ሞገዶቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ድል ካደረጉባቸው ሦስት መርሐ-ግብሮች በኋላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር መራራቃቸውን ተከትሎ ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ቀርተዋል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት የአቻ ውጤቶች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ባህርዳር ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ባስተናገዱበት መርሐ-ግብር ላይ ከ180′ ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም በጥቅሉ በዕለቱ የነበራቸው አፈፃፃም ደካማ መሆን ግን ትልቅ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ቡድኑ እጅግ ፈታኝ ከነበረው መሪው መድንን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ በተከታታይ ነጥብ መጣሉ ያልተጠበቀ ነበር፤ ለገጠመው የውጤት መቀዛቀዝ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ የፊት መስመሩ ውጤታማነት ማሽቆልቆል ሲሆን ቡድኑ በድምሩ ስምንት ግቦች ካስቆጠረባቸው ሦስት ጨዋታዎች በኋላ በተከናወኑ ሦስት መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የማጥቃት ጥምረቱ ውጤታማነት ምን ያህል እንዳሽቆለቆለ ማሳያ ነው። የአሰልጣኝ ደግአረገ ቡድን አሁንም የግብ ዕድሎች እየፈጠረ መቀጠሉ ጨርሶ ላልጠፋው የዋንጫ ዕድሉ ተስፋ ቢሆንም በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ትልቅ ዋጋ ያስከፈለውን የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል።
በሰላሣ ስድስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ሳይጠበቁ በአጭር የጨዋታ ሳምንታት ከገቡበት የስጋት ቀጠና ለመውጣት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።
በሰባት ሳምንታት ዕድሜ ውስጥ ከዋንጫ ተፎካካሪነት ወደ ላለመውረድ የሚደረገው ፍልሚያ ያሽቆለቆሉት አርባምንጭ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል። ድል ካደረገ ስምንት ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ከገጠሙት አራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በ31ኛው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ድል ማድረጋቸው ተከትሎ በሰንጠረዡ አንድ ደረጃ አሽቆልቁሎ ለወራጅ ቀጠናው ቀርቧል። በ15ኛ ደረጃ ላይ ካለው መቐለ 70 እንደርታ ጋር በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ እንደመሆናቸው በነገው ጨዋታ ድልና ድል ብቻ እያለሙ ወደ ሜዳ መግባት የሚጠበቅባቸው አዞዎቹ ከምንም ነገር በላይ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ድክመት ማረም ይኖርባቸዋል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ የማጥቃት ጥምረት ያላቸው አርባምንጭ ከተማዎች ጠንካራ የመከላከል ውቅር ካለው ተጋጣሚ ለሚጠብቃቸው ፈተናም ተገቢ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል የመስመር ተከላካዮቹ ግርማ ዲሳሳ እና አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይኖሩም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ ካለው በላይ ገዛኸኝ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ 3 ጊዜ ባህርዳር ከተማ ደግሞ 1 ጊዜ ድል ሲያደርጉ 1 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አዞዎቹ 4 የጣና ሞገዶቹ ደግሞ 3 ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።