ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ሦስት ነጥብን ከሦስት ጎል ጋር ከሲዳማ ቡና ላይ አሳክቷል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ሦስት ነጥብን ከሦስት ጎል ጋር ከሲዳማ ቡና ላይ አሳክቷል

ኢትዮጵያ መድኖች 3ለ0 በሆነ ውጤት ሲዳማ ቡናን በመርታት ተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ነገ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በዘጠኝ በማድረግ መሪነታቸውን አጠናክረዋል።

መድኖች በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገደው ቡድናቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉበት ሲገቡ ሲዳማ ቡናዎች ግን በአምስቱ ላይ ቅያሪን አድርገዋል። ጊት ጋትኩት ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ አበባየሁ ሀጂሶ ፣ ማይክል ኪፕሩቪ እና ሐብታሙ ታደሠን አርፈው ደስታ ደሙ ፣ ሬድዋን ናስር ፣ በዛብህ መለዮ ፣ ደግፌ አለሙ እና ይገዙ ቦጋለ ተክተዋቸው በቋሚ አሰላለፍ ገብተዋል።

መድኖች ከሽንፈት ወደ ድል ለመመለስ ሲዳማ ቡናዎች አሸናፊነታቸው ለማስቀጠል ወሳኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ፍፁም የእንቅስቃሴ እና የሙከራ የበላይነቱን በተጋጣሚያቸው ላይ መውሰድን ችለዋል። በ5ኛው ደቂቃ ከያሬድ ባዬ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ከቀኙ ሳጥን ደግፌ አለሙ አሻግሮ መስፍን ታፈሠ ቢያገኛትም የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ ቀድሞው መውጣት ታክሎበት ኳሷ ተጨራርፋ ወጥታለች።

በይበልጥ መሐል ሜዳውን በነፃነት በመጠቀም ወደ መስመር በተለጠጠ እንቅስቃሴ ውስጥ የቀጠሉት ሲዳማዎች 8ኛው ደቂቃም ይገዙ ቦጋለ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሞክሮ የግቡን ቋሚ ብረት ኳሷ ገጭታ ስትወጣ ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ በዛብህ መለዮ ሳጥን ውስጥ እጅግ ጠጣር ሙከራን ሰንዝሮ የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ ንቃት አምክኖበታል። በሲዳማ ቡና ከተወሰደባቸው ብልጫ ቀስ በቀስ ከአስራ አምስተኛው ደቂቃ በኋላ ወደ ጨዋታው የገቡት መድኖች በሽግግር አጨዋወት ወደ ሳጥኑ ደጋግመው በመጠጋት ጫናን ማሳደር ጀምረዋል።

16ኛው ደቂቃ ከዳዊት ተፈራ አለን ካይዋ ያገኛትን ኳስ ተፈጥሯዊ ባልሆነው ግራ እግሩ መቶ በቀላሉ ቶማስ ኢካራ የያዘበት 20ኛው ደቂቃም ዳዊት በጥሩ ዕይታ የሰጠውን በግምት ከሀያ አምስት ሜትር ርቀት አለን ሞክሮ የግብ ዘቡ ቶማስ ኢካራ የያዘበት አጋጣሚ በቡድኑ የተደረጉ ተከታታይ ዕድሎች ነበሩ። ከአጀማመራቸው አኳያ መጠነኛ መውረዶችን ያሳዩት ሲዳማዎች ያሬድ ካሳዬ ተሳስቶ በደረቱ የሰጠውን ፍቅረየሱስ ከሳጥን ውጪ መቷት አቡበከር ያወጣበት ኳስ እና ይገዙ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ከግብ ጠባቂው አቡበከር ጋር ተገናኝቶ መጠቀም ሳይችል ከቀረበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በኋላ በይበልጥ ጫናቸው ያየለው መድኖች 30ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል።

መነሻዋን ከቀኝ አድርጋ ወገኔ ለሀይደር ሰጥቶ መልሶ ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ መቶ መረብ ላይ አሳርፏታል። ማጥቃታቸውን እያሳደጉ የሲዳማን መከላከል በቀላሉ መፈታናቸውን የቀጠሉት መድኖች አቡበከር ሳኒ ከርቀት የመታት ኳስን ግብ ጠባቂው ኢካራ ነክቶ በማውጣቱ ወደ ማዕዘን ምትነት የተቀየረችዋን ኳስ ዳዊት 38ኛው ደቂቃ ሲያሻማ አቡበከር ሳኒ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር መድኖችን 2ለ0 መሪ አድርጓቸዋል።

ሲዳማ ቡናዎች ከዕረፍት መልስ ሬድዋን ናስር ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና አስቻለው ሙሴን በሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና አቤኔዘር አስፋው ቀይረው ቢመለሱም ከቆሙበት እንቅስቃሴያቸው የቀጠሉት ግን መድኖች ነበሩ። ሲዳማ ቡናዎች አዲስ የማጥቃት ጉልበትን ቢጨምሩም ከኋላ ክፍላቸው ላይ የሚታየው ዝንጉነት ግን በቀላሉ ተጋጣሚያቸው ጥቃቶችን እንዲሰነዝርባቸው ሆኗል።

 

በ54ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ በግቡ እና በግብ ጠባቂው ቶማስ ዕገዛ ከተመለሠችበት አደገኛ ሙከራ መልስ 66ኛው ደቂቃ አለን ካይዋ ከግራ በጥልቀት ገብቶ ወደ ውስጥ ያሻገራትን ኳስ ብርሀኑ በቀለ ራሱ መረብ ላይ አስቀምጧት  የመድንን የግብ መጠን ወደ ሦስት አሳድጓል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚመስልን ነገር ግን በሙከራ ረገድ መድኖች በአለን ካይዋ እና አብዲሳ ጀማል ያደረጉበት ቢሆንም ጨዋታው ግን ተጨማሪ ግቦች ሳይታዩበት በመድን 3ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ድሉም መድንን ከሽንፈት ወደ ድል በመመለስ ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ቡናማዎቹ ነገ እስኪጫወቱ ድረስ ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደረጉበትን ወሳኝ ውጤት በመያዝ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።