ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በነገው ዕለት ድል ማድረግ ካልቻለ ከሊጉ የሚሰናበተው ስሑል ሽረ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

በሀያ ሁለት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸው ነገ ይወሰናል፤ በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የማይችሉ ከሆነ የመውረዳቸው ጉዳይ ስለሚረጋገጥም በጨዋታው ድል  ማድረግ ግድ ይላቸዋል።

ከተከታታይ ስድስት የአቻ ውጤቶች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች ከደካማው የውድድር ዓመት በኋላ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ ተቃርበዋል። በ14ኛ ደረጃ ላይ ካለውና በአሁናዊው የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት በሊጉ ተራፊ ከሆነው ድሬዳዋ ከተማ በአስራ አራት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ብያንስ እስከ መጨረሻ ሳምንት ድረስ ላለመውረድ በሚደረገው ፍልምያ ለመቀጠል በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።

ቡድኑ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት መርሐ-ግብሮች ለትችት የሚዳርገው እንቅስቃሴ ባያደርግም ማሸነፍ አልቻለም። ሊጉ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘቱ መጠን እና ቡድኑ ካለበት ደረጃ መነሻነት ጥሩ በሆነበት አይደለም ጥሩ ባልተንቀሳቀሰበት ጨዋታም ድሎች እጅግ ወሳኝ ስለሆኑ ቡድኑ እንቅስቃሴውን በውጤት ማሳጀብ ይገባዋል። ቡድኑ ከቀሩት አምስት መርሐ-ግብሮች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ ሙሉውን ማግኘት ቢችልም በሊጉ ለመትረፍ የሌሎች ቡድኖች ውጤት ለመጠበቅ ስለሚገደድ አሁን ባለው ሁኔታ በሊጉ የመትረፍ ዕድሉ እጅግ ጠባብ ነው።

በአርባ ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግሞ ደረጃውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል።

በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር በወጥነት መዝለቅ ያልቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ጠንካራ ጎኖቹ ከድተውት ይገኛል። ቡድኑ በዙሩ በሁለት አጋጣሚዎች ሦስት ተከታታይ፤ በአንድ አጋጣሚ ደግሞ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱም ወደ ጨዋታዎች የሚቀርብበት እና የሚከውንበት መንገድ ብዙ ስህተቶች እንዳሉበት ማሳያ ነው። እርግጥ ቡድኑ በመሀል ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርጎ ደረጃውን ማሻሻል ቢችልም ቀጥለው በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ግን በመደዳ ሽንፈት አስተናግዷል። በመርሐ-ግብሮቹም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበራቸው ድክመት ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ፈረሰኞቹ ባለፉት ሦስት መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠራቸው እንዲሁም አራት ግቦችን ማስተናገዳቸውም በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ረገድ ላሉባቸው ድክመቶች ማሳያ ነው። በተለይም በቅርብ ሳምንታት በግብ ጠባቂዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የተስተዋለው ተሻጋሪ ኳሶችን የመመከት እንዲሁም የቦታ እና ጊዜ አጠባበቅ ስህተቶች ቡድኑን ዋጋ አስከፍለውታል።

በስሑል ሽረ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ከክለቡ ማግኘት ባንችልም ቡድኑ በነገው ዕለት በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች እንደሌለ አረጋግጠናል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማኑኤል ኤርቦ በቅጣት ተገኑ ተሾመ በጉዳት ካለመኖራቸው ውጭ የተሟላ ስብስቡን ይዞ የሚቀርብ ይሆናል።

በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 3 ጊዜ ተገናኝተው ጊዮርጊስ 2 ጨዋታ አሸንፎ በተቀረው አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ግቦች ማስቆጠር ሲችል ስሑል ሽረ ግን ግብ ማስቆጠር አልቻለም።