በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች ከስጋት ቀጠናው ለማምለጥ የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከስድስት የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ በተመሳሳይ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ የሚያልሙትን ድሬዳዋ ከተማዎች ይገጥማሉ።
በ25ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፉ በኋላ በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ንግድ ባንኮች በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ለስጋት ቀጠናው ቀርበዋል። በወራጅ ቀጠናው ዙርያ የሚገኙ ተከታዮቻቸው ድል እያስመዘገቡ የነጥብ ልዩነቱን ማጥበባቸውም ቡድኑ በነገው ዕለት ድልና ድልን እያለመ ወደ ሜዳ እንዲገባ የሚያስገድደው ጉዳይ ነው። ከተከታታይ አራት የአቻ ውጤቶች በኋላ በአዳማ ከተማ ሽንፈት ባስተናገዱበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ በወትሮ ብቃታቸው ያልነበሩት ሀምራዊ ለባሾቹ በዕለቱ ከዚህ ቀደም የቡድኑ መገለጫ የነበረው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ካለማስቀጠላቸው ባለፈ
የማጥቃት አጨዋወታቸው በብዙ ረገድ መሻሻል እንዳለበት የታየበት ነበር። በተለይም በውድድር ዓመቱ ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት ያልቻለው እና በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ በነገው ዕለት በተሻለ ብቃት መገኘት ግድ ይለዋል።
በሰላሳ ስድስት ነጥብ 14 ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና ዛሬ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሸነፉን ተከትሎ በሰንጠረዡ በአንድ ደረጃ ዝቅ ለማለት የተገደደው ድሬዳዋ ከተማ ራሱን ለማትረፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ተስፋ የሚሆኑ ነጥቦችን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል።
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ መልካም እንቅስቃሴ አድርገው በመደዳ ወሳኝ ድል የተቀዳጁት ብርቱካናማዎቹ ውጤቶቹን ተከትሎ ከከፋ የመውረድ ስጋት በመጠኑ እፎይታ ማግኘት ቢችሉም የቅርብ ተፎካካርያቸው ኤሌክትሪክ ዛሬ ድል ማድረጉ እና ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀር ላይ መገኘታቸው ነገ አሸንፈው ከመቐለ ጋር ያላቸውን ርቀት ወደ ስድስት ለማስፋት እያለሙ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ከታየው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በተለየ የድል ረሀብ ወደ ጨዋታዎቹ የቀረቡት ብርቱካናማዎቹ
ላለመውረድ እያደረጉት ባለው ፍልምያ ውስጥ እንደ ቡድን እየታየባቸው ያለው ጠንካራ የተነሳሽነት መንፈሳቸው ማስቀጠል ይኖርባቸዋል። እንደ ባለፈው ሳምንት ነገም ድል ከቀናው 13ኛ ደረጃነት ለኤሌክትሪክ አስረክቦ ብያንስ አንድ ደረጃ የማሻሻል ዕድል ያለው ቡድኑ ከላይ የተጠቀሰውን ጥንካሬ ከማስቀጠል ባለፈ በመጨረሻው ጨዋታ ከሰባት መርሐ-ግብሮች በኋላ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረው እና ለጠንካራው ተጋጣሚው ፈተና በነበረውን የማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ መዝለቅ ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብሩክ እንዳለ ከሁለት ጨዋታ ቅጣት ሲመለስ ባሲሩ ኡማር አሁንም በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። የተቀሩት የቡድኑ አባለት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። ድሬዳዋ ከተማዎችም ከመሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው አምስት አምስት ጊዜ ሲሸናነፉ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 28 ጎሎች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ 2 ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ባንክ 15፣ ድሬ 13 ጎሎችን አስቆጥረዋል።