ሱፐር ስፖርት የሊጉን ጨዋታዎች ሊያስተላልፍ ነው

ሱፐር ስፖርት የሊጉን ጨዋታዎች ሊያስተላልፍ ነው

ለአምስት አመታት የሊጉን የምስል መብት የገዛው ሱፐር ስፖርት በመጨረሻዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች እንደሚመለስ ተሰምቷል።

ግዙፉ የቴሌቪዥን ተቋም ሱፐር ስፖርት የሀገራችንን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የስያሜ እና የምስል መብት በመግዛት ያለፉትን አመታት ግልጋሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል። በውሉ መሠረት በመጨረሻው ዓመት ላይ የሚገኘው ሱፐር ስፖርት ዘንድሮ እንዳለፉት ዓመታት በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ያላስተላለፈ ሲሆን በግዴታው መሠረት ማስተላለፍ ያለበትን የ60 ጨዋታዎች ቁጥር ለተመልካቾች እንደሚያደርስ ተገልጾ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለመጨረሻ ጊዜ የመጀመሪያውን ዙር የመጨረሻ ሁለት ሳምንታት ያስተላለፈው ተቋሙ መቼ ወደ ስርጭት ይመለሳል የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን ሲያነጋግር የቆየ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም በጉዳዩ ዙሪያ ማጣራት አከናውና የሊጉ ጨዋታዎች መቼ መተላለፍ እንደሚጀምሩ አረጋግጣለች።

በዚህም መሠረት የፊታችን ሰኞ ከሚጀምረው 33ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ 36ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ተቋሙ ውሳኔ ላይ መድረሱን እና ለቀጥታ ስርጭቱ አስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ሰምተናል።