በአምስት ነጥቦች እና በስድስት ደረጃዎች የሚበላለጡ ቡድኖች ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ ቀትር ላይ ይካሄዳል።
በአርባ ሦስት ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ከተከታታይ አምስት የአቻ ውጤቶች በኋላ ድል ማድረግ የአንድ ደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።
ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት መቻሎች ባለፉት መርሐ-ግብሮች ከድል ጋር መራራቃቸውን ተከትሎ ወደ መሪዎቹ የሚጠጉበትን ዕድል አባክነዋል። ቡድኑ በ22ኛ እና 23ኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ በፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና ከገጠሙት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግሞ ብያንስ ከሽንፈት መራቁ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም በሜዳ ላይ የሚያሳየውን መልካም እንቅስቃሴ ወደ ውጤት መቀየር ተስኖታል። ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ በተጋራበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ የተስተዋለውም ይህ ነው፤ ቡድኑ በዕለቱ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለመጠበቅ ተገዷል።
የነገ ጨዋታ ማሸነፍ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ ብያንስ የውድድር ዓመቱ የተሻለ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በር ስለሚከፍትለትም በተለይም በአፈፃፀም ረገድ የሚታይበትን ክፍተት ማረም ይኖርበታል።
በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ያሳዩት አስደናቂ መሻሻል ከወራጅ ቀጠናው አልፎ በሰንጠረዡ አማካይ ላይ እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል። በነገው ዕለት ድል ማድረግም ከስጋት ቀጠናው ያለውን ርቀት በማስፋት ይበልጥ ስለሚያረጋጋው መርሐ-ግብሩ ወሳኝ ነው።
በመሪው መድን ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች እጅ ያልሰጡት ሀይቆቹ በተጠቀሱት የቡድኑ የሊጉ ህልውና ላይ ወሳኝ በነበሩ መርሐ-ግብሮች ውስጥ አምስት ድልና ሦስት የአቻ ውጤቶች ከማስመዝገብ በላይ በሜዳ ላይ የነበረው ውጤታማነት አድናቆት የሚያስቸረው ነው። ዓሊ ሱሌይማንን ጨምሮ ፈጣኖቹ የፊት መስመር ተጫዋቾች ላይ መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ አጨዋወት የሚከተሉት አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት ከውጤታማው የፊት መስመር ጥምረታቸው በተጨማሪም ባለፉት ስምስት ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ያላስተናገደ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ችለዋል። በነገው ዕለት ግን ባለፉት ስምንት መርሐ-ግብሮች ሽንፈት ያላስተናገደ እና በጨዋታዎቹ አራት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ቡድን እንደመግጠማቸው በውጤታማነቱ ለመዝለቅ በሁሉም ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየት ግድ ይላቸዋል።
መቻል በወላይታ ድቻው ጨዋታ ያጣው አብዱልከሪም ወርቁ ከጉዳት ቢመለስለትም አምበሉ ዳዊት ማሞ በጉዳት ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ አሊዮንዚ ናፊያን ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ምክንያት በነገው ጨዋታ ግልጋሎት አይሰጡትም። በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ በአወዳዳሪው አካል በተጣለበት ቅጣት ምክንያት ለቀጣዮቹ አራት ጨዋታዎች ከሜዳ የሚርቅ ሲሆን ፈቃደስላሴ ደሳለኝ ከቅጣት ይመለሳል።
ሁለቱ ቡድኖች 35 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ ከተማ 15 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መቻል 10 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 81 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 44 መቻል በበኩሉ 37 ጎሎችን አስቆጥረዋል።