ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

33ኛው ሳምንት አዳማ ከተማ ከ14 የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ደረጃውን አሻሽሎ የመትረፍ ዕድሉን ለማለምለም ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግሞ ደረጃውን ለማስከበር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።

በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበትን ዕድል ያለመለሙት አዳማ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል።

በመሃል በኢትዮጵያ ቡና ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ በቅርብ ሳምንታት ከሽንፈት የራቁት አዳማ ከተማዎች ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ድል፣ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ በመልካም አቋም ይገኛሉ፤ ሆኖም ቡድኑ አሁንም በአደገኛው ቀጠና ስለሚገኝ በቀጣይ ሳምንታት ለመትረፍ በሚያደርገው ትንቅንቅ ውስጥ ነገ ድል ማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉም መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ ከአስራ አራት የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ አንድ ደረጃ የማሻሻል ዕድል ከማግኘታቸውም በላይ በ14ኛ ከተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ማጥበብ የሚችሉ በመሆኑ ውጤቱን እጅግ አጥብቀው ይፈልጉታል።

ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ባሸነፈበት የመጨረሻው ጨዋታ ላይ በሁሉም ረገድ በሚባል መልኩ ከተጋጣሚው የላቀ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም ዕድሎችን የመጠቀም ድክመቱን ግን አሁንም ጨርሶ አልቀረፈም፤ በተለይም የተሻለ ብልጫ በወሰደበት የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎችን አምክኗል። የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ቡድን ከባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን በማስከበር የውድድር ዓመቱ ቀንደኛ ድክመቱ የነበረውን የመከላካል ድክመት መቅረፉ፤ አሁንም የግብ ዕድሎችን እየፈጠረ መዝለቁ እንዲሁም ቡድኑ ላይ የታየው መነሳሳት በአወንታነቱ የሚጠቀስ ቢሆንም ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር በነገው ዕለት እንደ ባለፉት መርሐግብሮች በርከት ያሉ ዕድሎች ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም፤ ስለዚህ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉት ዕድሎችን የመጠቀም ክፍተቱን ማረም ይኖርበታል።

በአርባ ስምንት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና ከድል ከራቀ አራት ጨዋታዎች የሆኑት ባህር ዳር ከተማ የቅርብ ሳምንታት ደካማ አቋሙ ከመሪዎቹ እያራቀው ይገኛል።

መሪው መድንን ካሸነፉ በኋላ በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ሁለት የአቻ እና ሁለት ሽንፈቶች የገጠማቸው የጣና ሞገዶቹ በድሬዳዋ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ከደረሱባቸው ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ድል ማድረግ ደረጃቸውን እንዲያስከብሩ ይረዳቸዋል። በቅርብ ሳምንታት የቀድሞ ጥንካሬውን ማስቀጠል ያልቻለው ቡድኑ በተለይም በፊት እና ኋላ የተስተዋሉበት ድክመቶች ለውጤት መጥፋቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። የተከላካይ ክፍሉ በ17ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሦስት ለአንድ ከተሸነፈበት ጨዋታ ውጭ በውድድር ዓመቱ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስተናግድ ከዘለቀ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በመደዳ ሁለት ሁለት ግቦች ማስተናገዱ እንዲሁም የማጥቃት ክፍሉ በሦስት መርሐግብሮች ስምንት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘቱም በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ ላሉባቸው ድክመቶች ማሳያዎች ናቸው። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ቡድኑ በዋናነት ግቦችን ስለሚያስቆጥርበት እና የመከላከል አደረጃጀቱ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው የሚመልስበት መንገድ አጥብቆ ማሰብ የሚገባው ይመስላል።

በአዳማ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ፣ መሳይ አገኘሁ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄ ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 7 በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አዳማ 3 አሸንፎ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 13 ሲያስቆጥር አዳማ 6 አስቆጥሯል።