ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

መቐለ 70 እንደርታ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ከሊጉ ላለመውረድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ የቅርብ ዓመታት የውጣ ውረድ አካሄዱን ላለመድገም የሚፋለሙት እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ከሊጉ የሚወርድ ቡድን ይለይበታል።

በሊጉ ለመቆየት ድልና ድል ብቻ የሚያስፈልጋቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ሊጉ ካደጉበት 2010 ዓ.ም በኋላ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ከፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ ብርቱ ፍልምያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በወንጂ በተካሄደው የመጨረሻው ጨዋታ ላይ ወልዋሎን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቐርቡት መቐለ 70 እንደርታዎች በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች እጅ አልሰጡም። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስራ አንዱን በማሳካት በሊጉ የመትረፍ ዕድሉን ያለመለመው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በሜዳ ላይም ሆነ በመንፈስ ረገድ የሚታይ መሻሻል ማሳየቱ ባይካድም በነገው የክለቡ የሊጉ ቆይታ በሚወስነው እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ላይ በብዙ ረገድ የላቀ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ ይለዋል። የቡድኑ ቀዳሚ ድክመት ሆኖ የዘለቀው የግብ ዕድሎች የመፈፀም ችግር እና በተጋጣሚ የግብ ክልል አከባቢ ያለበትን ውስንነት መቅረፍ ደግሞ ዋነኛ ዓላማው መሆን ይገባዋል።

የነገው ተጋጣሚያቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የገነባ እና በስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን አስከብሮ ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ እንደመሆኑ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሊጉ ለመቆየት ድልና ድል ብቻ የሚያስፈልገው ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የሚያሳየው ብቃት ወሳኝነቱ ትልቅ ነው፤ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ጫና ውስጥ ላለመግባት ደግሞ በሊጉ ለመቆየት የአቻ ውጤት ብቻ የሚያስፈገውን ተጋጣሚው ላይ ቀድሞ ብልጫ መውሰድ ግድ ይለዋል።

በአርባ አንድ ነጥብ የነገ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የባለፉት ዓመታት የውጣ ውረድ አካሄዱን ላለመድገም ከቅርብ ተፎካካሪው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ይፋለማል።


የ2010 እና የ2015 ዓ.ም ከሊጉ የመውረድ ታሪኩን ላለመድገም በነገው ጨዋታ ነጥብ መጋራት በቂው የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ እጅግ ወሳኝ መርሐ-ግብር ላይ ብያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የቅርብ ሳምንታት እንቅስቃሴውን ይበልጥ ማዳበር ይኖርበታል።

ቡድኑ ከ27ኛ እስከ 29ኛ ሳምንት ላይ በተከናወኑ መርሐ-ግብሮች ላይ በመደዳ ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ በመቅመስ ሦስት የአቻ እና ሁለት ድሎች በማስመዝገብ የመትረፍ ዕድሉን ማለምለም ቢችልም እንቅስቃሴው ግን በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ነው። እርግጥ ቡድኑ ባለፉት ስድስት መርሐ-ግብሮች ላይ በአራቱ መረቡን አስከብሮ ሁለት ግቦች ብቻ ማስተናገዱ በአወንታነቱ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም በጨዋታዎቹ ላይ የነበረው ተጋላጭነት ግን በነገው ፍልምያ የሚያሰጋው ነገር ነው። የነገው ተጋጣሚያቸው በሊጉ ለመትረፍ ድል ማድረግ ግድ የሚለው መሆኑም ምናልባትም ጠንካራ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታ የሚቆጣጠሩበት አኳኋን ማስተካከል እንዲሁም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመራቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

በጥቅሉ ሲታይ በቅርብ ሳምንታት የቡድኖቹ አቀራረብ እንዲሁም ኤሌክትሪክ በሊጉ ለመቆየት አንድ ነጥብ ብቻ በቂው በመሆኑ ምናልባትም መቐለ ከፍ ባለ ማጥቃት ኤሌክትሪክ ደግሞ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይገመታል።

በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ተከላካዩ መናፍ ዐወል በጉዳት ምክንያት የማይሰለፍ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች የለም።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው ሦስቱንም መቐለ 70 እንደርታ አሸንፏል። በግንኙነቱ መቐለ 4 ግቦች ስያስቆጥር ኤሌክትሪክ 1 አስቆጥሯል።