የዋንጫ ያክል ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኢዮብ ገብረማርያም ግብ ብቸኛ ግብ ምዓም አናብስትን በማሸነፍ በሊጉ የሚቆዩበትን ትኬት መቁረጥ ችለዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጨረሻው ሳምንት የዋንጫ ያክል ተጠባቂ የሆነውን ላለመውረድ የሚደረግ ጨዋታ ምሽት 12:00 ሰዓት ሲል በአ.ሳ.ቴ.ዩ ስታዲየም የሰሜኑ ተወካይ መቐለ 70 እንደርታን ከ መዲናው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አገናኝቷል።
መቐለ 70 እንደርታዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወልዋሎ ዓዲግራትን ካሸነፉበት አሰላለፍ ሰለሞን ሐብቴ እና አሸናፊ ሐፍቱን በማሳረፍ በምትካቸው መድሃኔ ብርሃን እና ቦና ዓሊን ሲያስገቡ በተመሳሳይ መቻል ላይ ጣፋጭ ድልን ተጎናጽፈው የመጡት ኤሌክትሪኮች ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ብቻ ተጫዋች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ጌታሁን ባፋን በአብዱላሂ አልዩ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ብዛት ባላቸው የደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወ/ፃዲቅ መሪነት የተጀመረው ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስመልክቶናል። 4ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በግንባሩ ጨርፎ ወደ ወደ ግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በጥሩ እይታ አሻሞቶ ኢዮብ ገብረማርያም በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ በመሆን ጥሩ ጅማሮን ማድረግ ችለዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ብልጫ የወሰዱበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን የመስመር አጥቂዎቻቸውን ዒላማ ባደረጉ ኳሶች ግቦችን ደግመው ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ በተቃራኒው መቐለዎች ባልታሰበ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ ምክንያት መረጋጋት ያልቻሉ ሲሆን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ነገር ግን ግቦችን ለማስቆጠር ተቸግረው በኢትዮ ኤሌክትሪኮች 1-0 መሪነት አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ወደ ግብ በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ሲሆን 59ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር ተጨርፎ በነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው ቦና ዓሊ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ የመታው ቢሆንም ዒላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጭ ወጥቷል። ይህም ለመቐሌዎች አስቆጪ ሙከራ ነበር።
ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ የዘለቀው ይህ ጨዋታ ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት ጫናዎችን በመፍጠር ወደ ፊት ገፍተው የሚጫወቱት መቐለ 70 እንደርታዎች 84ኛው ደቂቃ ላይ ለግቡ ቅርብ በሆነ ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ቦና ዓሊ ወደ ግብ ቢመታውም በግብጠባቂው ኢድሪሱ አብደላሂ ድንቅ ማዳን ምክንያት ግብ ከመሆን ድኗል።
መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ መቐለ 70 እንደርታዎች እጅግ አስቆጪ የሆኑ ሁለት ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ቤንጃሚን ኮቴ የግብ ጠባቂው ኢድሪሱን ስህተት ተጠቅሞ የመታውን ኳስ አብዱላሂ አልዩ ከመስመር ላይ መልሶ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል። እንዲሁም ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ቀጣይ አመት በሊጉ ቆይታቸውን ሲያረጋግጡ በተቃራኒው መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመቐለ 70 እንደርታው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም “በጨዋታው ጅማሮ የገባብን ግብ መረጋጋት እንዲጎለን እና ያሰብነውን ነገር እንዳናደርግ አድርጎናል ለዚህም ደጋፊዎችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። በመቀጠልም ህጉን አክብረን እስካሁን ቆይተናል ስለዚህ ያሉብንን የህግ ጥያቄዎች ተከትሎ ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔ እንጠብቃለን።” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው “በልጆቼ ጥረት ምክንያት ይህንን ጨዋታ አሸንፈን በቀጣዩ አመት በሊጉ በመቆየታችን ደስተኛ ነኝ ለዚህም ተጫዋቾቼን አመሰግናለሁ።” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።