የከሰረው ዓመት !

የከሰረው ዓመት !

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የክፍያ ስርዓቱን የጣሱ ክለቦችን የተመለከቱ ውሳኔዎች ማስተላለፉ ይፋ አድርጓል። ስራ አስፈፃሚው የወሰነው ባለ አስር ነጥብ ውሳኔ ይፋ ከሆነ በኋላም የእግር ኳስ ማሕበረሰቡን በሁለት ጎራ ከፍሎ ያከራከረ ጉዳይ ሆኗል።

የሊጉ አወዳዳሪ አካል አርቅቆት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይሁንታ የፀደቀው አዲስ የክፍያ ስርዓት መዘርጋቱ እንደ አወንታ የሚጠቀስ ነጥብ ቢሆንም ሂደቱ ግን የእግር ኳሱን አስተዳዳሪ አካላት የውሳኔ ማስፈፀም አቅም እና ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል። አጠቃላይ በእግር ኳሳችን ላይ ከውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች ስር የሰደዱ እና በርከት ላሉ ጊዜያት የቆዩ ቢሆንም በተጠናቀቀው ዓመት የተስተዋሉት ርትዕ የጎደላቸው፣ በጣም ብዙ ውዝግብና ሽኩቻ  ያስከተሉ ምሉዕነት የሌላቸው ደካማ ውሳኔዎች ግን  ውድድር ዓመቱን በኪሳራ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል።

በስራ አስፈፃሚው የትናንትናው ዕለት ውሳኔ ተራ ቁጥር 3 ላይ የፍትህ አካላት ውሳኔ በመደበኛ ፍርድ ቤት በማሳገድ መሰለፍ የሌለባቸው የታገዱ ተጫዋቾች ተጠቅመው ያገኟቸው ነጥቦች በሙሉ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆኑ የወሰነ ቢሆንም በተራ ቁጥር 10 የተጠቀሰው የ2018 ውድድር ዓመት በ20 ክለቦች እንዲከናወን የተወሰነበት ውሳኔ ግን ራሱ አወዳዳሪው አካል ያወጣውን ህግ የጣሱ ክለቦች የሚያስታምም፣ ህጉን አክብረው ዓመቱን ሙሉ ተገዢ የነበሩትን ክለቦችን ልፋት እውቅና የማይሰጥ እና በፍትሕ አካላትና ሂደቱ ላይ እምነት ማጣትን የሚያስከትል ሆኗል።

የተንዛዛው የክፍያ ስርዓቱን የማጣራት ሂደትና ርትዕ የጎደለው ውሳኔ የ2017 የውድድር ዓመት በኪሳራ እንዲጠነቀቅ ከማስቻሉም በላይ የቀጣይ ውድድር ዓመት የሚያስከትለው መዘዝም እንዲው በዋዛ የሚታለፍ አይደለም። የተወዳዳሪ ክለቦችን ቁጥር መጨመር ተከትሎ በእያንዳንዱ ተሳታፊ ክለቦች የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጫና፣ እውን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ክለቦቹም ሆነ አወዳዳሪው አካል ለ38 ሳምንታት የሚዘልቅ የውድድር ዓመት ማስተዳደርና እና ለመሳተፍ የሚያስችል ጫንቃ አላቸው የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በእያንዳንዱ  አዘጋጅ ከተሞች የሚገጥመው የስታዲየም እና የልምምድ ሜዳ እጥረት ችግሮች ሳይረሳ።

ከዚህ በተጨማሪ ውሳኔው አጠቃላይ የሀገሪቱ የሊጎች ‘pyramid’ ላይ መፋለሶች የሚስከትል ነው። በውሳኔው በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ሊግ አንድ፣ ከሊግ አንድ ወደ ክልሎች ሻምፒዮና ስለወረዱ ክለቦች የተጠቀሰ ነጥብ የለም፤ ስለዚህ በዋናው ሊግ ብቻም ሳይሆን በታችኞቹ ሊጎች ላይም የህግ ጥሰት መፈፀሙ አይቀሬ ይመስላል። ለአብነት በቅርቡ በሊግ አንድ ውድድር ዓመቱን ሙሉ ሦስት ክለቦች ብቻ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንደሚያድጉ ሲገለፅ ቆይቶ በ11ኛው ሰዓት ለዛውም በማጠቃለያ ጨዋታዎች የፍፃሜ እና የደረጃ ጨዋታ ቀን ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦች ከ3 ወደ 4 እንዲሆን መደረጉ ተገልጿል። ከምን መነሻነት የመጣ ለውጥ መሆኑ ባይታወቅም ከተቀመጠ ህግ ውጪ በ11ኛ ሰዓት የሚመጡ የህግ ለውጦች በግብታዊነት የተወሰኑ እንደሆነ ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ በተዋረድ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው አካላት ይኖራሉ።

ቀደም ብለው ከተጠቀሱት ስጋቶች በላቀ ምናልባትም ትልቁ ስጋት መሆን የሚችለው ግን ሕግን ጥሰዋል የተባሉ አካላት ባልተቀጡበት ሁኔታ ክለቦች ከአሁን በኋላ በምን አይነት መንገድ ለሕግ ተገዢ ሆነው ይቀጥላሉ? በፍትሕ አካላት፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ በአዳዲስ ሕጎግ አተገባበር ላይ ያለው እምነትስ እስከምን ድረስ ይሆናል?  በትልቁ ደሞ በአወዳዳሪ አካላትና ተወዳዳሪዎች ያለው መተማመንንስ? በጥቅሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከመልሶች ይልቅ ጥያቄዎች የበዙበት እንቆቅልሽ ሆኖ መዝለቁ እሙን ነው።